የተገኘዉ አንጻራዊ ሰላም የተሟላ እንዲሆን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከሀሰት ፕሮፓጋንዳ ራሱን በማራቅ የህግ የበላይነት የተረጋገጠበት ክልል ለመገንባት በጋራ መረባረብ እንደሚያስፈልግ የአማራ ክልል መንግስት ገለፀ፡፡
የአማራ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ባወጣው መግለጫ፤ የህግ የበላይነት መረጋገጥ የአንድን ማህበረሰብ የተረጋጋ ዘላቂ ህይወት ለመመስረትና ለመጭዉም ትዉልድ የሚተርፍ አሻራ ለማኖር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሶ፤ የክልሉ መንግስት ህግ ማስከበር ዋነኛ ግብ የህዝብን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
የአማራ ክልል መንግሥት ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ህግ ማስከበር ዋነኛ ግቡ የህዝብን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ ነዉ!
የህግ የበላይነት መረጋገጥ የአንድን ማህበረሰብ የተረጋጋ ዘላቂ ህይወት ለመመስረትና ለመጭዉም ትዉልድ የሚተርፍ አሻራ ለማኖር ወሳኝ ነዉ።
በግጭት ውስጥ የቆየ ማህበረሰብ ለህይወቱ፣ ለንብረቱና አጠቃላይ የኑሮዉ ዋስትና ስለማይኖረዉ የእለት ልብሱንና ጉርሱን ከመሻት አልፎ የዘላቂ ልማት አላማን ታሳቢ ያደረገ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ዉስጥ ሊሰማራ አይችልም።
ህገ-ወጥነትንና ስርዓት አልበኝነት እንደህዝብ አለመረጋጋትን የሚያስከትል በመሆኑ መቆጣጠር ካልተቻለ ሁሉንም ነገር ደረጃ በደረጃ ከመንግስትና ከህዝብ እጅ እንዲወጣ ያደርጋል።
ይህ ሁኔታ እንዳይፈጠር እና ሲፈጠር ለመቆጣጠር መንግስት የሚጠበቅበትን ህግ የማስከበር ስራ ይሰራል።
እዉነታዉ ይህ ሁኖ እያለ አንዳንድ አጥፊ ቡድኖችና ግለሰቦች የመንግስትን ሆደ ሰፊነት ቦታ ባለመስጠት በህዝብ ላይ ያልተገባ ህገወጥ ተግባር ሲፈጽሙ ይታያሉ።
እነዚህ ቡድኖች እና ግለሰቦች ራሳቸዉን ከህግ በላይ በማድረግ በተለያዩ ቦታዎች ያልተገባ ተግባር ከመፈጸም ባለፈ መንግስት የእለት ተእለት ተግባሩን ለህዝብ እንዳያደርስ እንቅፋት እየፈጠሩ ቆይተዋል።
በጽንፈኞች መሪ ተዋናኝነት በክልላችን በቅርብ ያጋጠመዉ የሰላም መደፍረስ ምክንያት የዜጎች እንቅስቃሴ የተገታበት፣ የመንግስት ተቋማት ስራ የተስተጓጎለበትና የተዘረፉበት፣
ከሁሉ በላይ አዉቀዉም ይሁን ሳያዉቁ የክልላችን ወጣቶች የጽንፈኞች ሀሳብ ተሸካሚ ሁነዉ የህይወት ዋጋ የከፈሉበትን ሁኔታ አስተናግደናል።
ይህ እኩይ ተግባራቸዉም በጀግናዉ መከላከያ ሰራዊታችን እና በክልላችን የጸጥታ ሀይል በጋራ በሰሩት ታሪካዊ ተግባር ፍላጎታቸዉ ሳይሳካ መክኗል። ይሁን እንጅ ይህ አጥፊ ቡድን የራሱን ግፍ እንደቅዱስ ተግባር በመቁጠር የመከላከያ ሰራዊታችን ምት መቋቋም ሲያቅተዉ የንጹሀንን ካባ ለብሶ ሙሾ ማዉረድ ዛሬም የዘለቀዉ የእለት ከእለት ተግባሩ አድርጎታል።
የዚህ እኩይ ተግባሩ ዋነኛ ማሳለጫዉም ከዉጭና ከዉስጥ በተዘረጋ የጥፋት ኔትወርክ ተጠቅሞ እየተወሰደበት ያለዉን ህግ የማስከበር ዘመቻ ህዝብ ውስጥ በመወሸቅና ራሱን የህዝብ ብቸኛ ጠበቃ በማስመሰል ማስተጓጎል ነዉ። የቡድኑ ባህሪም ሲመታ የንጹሀን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ አረመኒያዊ ተግባሩን ሲፈጽም ደግሞ እንደጀብዱ የሚቆጥሩ አጥፊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ማራገብ ነዉ።
በአሁኑ ወቅት ጽንፈኛ ቡድኑ ሴራዉ በአደባባይ ተገልጦበት፤ ጉልበቱ ከድቶት አለኝ የሚለዉን ገዥ ቦታ ሳይቀር ለመከላከያ ሰራዊታችን እና ለክልላችን የጸጥታ ሀይል በማስረከብ በየጉሬዉ ተደብቆ ይገኛል። ቡድኑም አንዳንዴ ከተደበቀበት ጉሬ በመዉጣት የዉጭና የዉስጥ ደጋፊዎችን አለሁ ለማለት ብቻ እኩይ ተግባሩን እየፈጸመ ይገኛል።
በክልላችን የተጀመረው ህግ ማስከበር ስራም ዋና ዓላማዉም የህዝብን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ታልሞ የሚተገበር በመሆኑ በቀጣይም ህግ የማስከበር ስራዉ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። ለዚህም ህብረተሰቡ ከመንግስት የፀጥታ መዋቅር ጎን ሆኖ ድጋፉን አጠናክሮ በመቀጠሉ አመርቂ ዉጤቶች ተመዝገባዋል።
በዉጤቱም በአብዛኛዉ የክልላችን አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል።
በተገኘዉ አንጻራዊ ሰላምም በጸጥታ መደፍረስ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸዉን መሰረተ-ልማትና ተቋማት ከመጠገን በተጨማሪ የክልሉን ህብረተሰብ ሁለንተናዊ እድገት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በመሆኑም የተገኘዉ አንጻራዊ ሰላም የተሟላ እንዲሆን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከሀሰት ፕሮፓጋንዳ ራሱን በማራቅ የህግ የበላይነት የተረጋገጠበት ክልል ለመገንባት በጋራ መረባረብ ይኖርበታል። በቀጣይም ልማቱን አጠናክሮ ለማሰቀጠልና ሰላምን ለማረጋገጥ ውስጣዊ አንድነትንና የዉስጥ ሰላምን የበለጠ ማጽናት ይገባል፡፡