የአዲስ ወግ የውይይት መድረክ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክና ከፖሊሲ ግብዓትነት አኳያ ምን አበርክቶ ነበረው?

1 Mon Ago
የአዲስ ወግ የውይይት መድረክ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክና ከፖሊሲ ግብዓትነት አኳያ ምን አበርክቶ ነበረው?

ለ5 ዓመታት የተካሄዱ የአዲስ ወግ መድረኮችን የሰነደው መፅሐፍ ዛሬ ሲመረቅ የተለያዩ አካላት ሀሳቦችን አንስተዋል።

የታሪክ ምሁሩ ዶክተር ታምራት ኃይሌ፥ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ አኳያ መንግሥት በአደባባይ ካካሄዳቸው ሀገራዊ የክርክርና የውይይት መድረኮች አንፃር የአዲስ ወግን ልዩ ገጽታ ቃኝተዋል።

በኢትዮጵያ ታሪክ በ17ኛው ክፍለ ዘመን በአጼ ሱስኒዮስ እንዲሁም በ19ኛው ክፍለ ዘመን በአጼ ዮሐንስ ዘመነ መንግስታት የነበሩ ሀይማኖት ነክ ክርክሮችን ከቀደምት የአደባባይ ውይይቶች ለማሳያነት ጠቅሰዋል።

በ20ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ ከ1917 እስከ 1928 ዓ.ም በስልጣኔ፣ ልማትና ትምህርት ጉዳዮች በብርሐንና ሰላም ጋዜጣ እንዲሁም በ1968 ዓ.ም ለጥቂት ወራት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የተደረጉት አብዮታዊ የክርክር መድረኮችን አንስተዋል።

"የሚያስመካ የውይይትና ክርክር ታሪኮች ነበሩን ማለት አያስደፍርም" ያሉት ዶክተር ታምራት፤ በታሪክ የተጠቀሱት መድረኮች በአጭር ጊዜ የተቋረጡና አሳታፊነታችውም የላላ ነበር ብለዋል።

በነጠላ እና በአንድ ወቅት ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ፣ በመንግሥታት ሳንሱር የተቋረጡ፣ በተሳታፊዎች በኩል የእርስ በርስ መጠራጠርና አለመተማመን የነበረባቸውና አሳታፊ የፖለቲካ ምህዳርም ያልነበራቸው ናቸው ነው ያሉት።

ከዚህ አንፃር የአዲስ ወግ መድረክ በመንግስሥት አነሳሽነት በክፍለ ዘመኑ ከተደረጉ የአደባባይ ውይይቶች የተለየ መልክ እንዳለው ገልጸዋል።

በወጥነትና ዘላቂ በሆነ መልኩ በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በአሳታፊነትና በሀሳብ ብዝሃነት ታጅቦ የቀጠለ መድረክ በመሆኑ ልዩ መልክ ነበረው ሲሉ አስረድተዋል።

የአዲስ ወግ ውይይቶች በመፅሀፍ መልክ መሰነዳቸውም የፖለቲካ ችግሮችን ሀሳብን መሰረት ባደረገ የውይይት መድረክ ለመፍታት ትልቅ ግብዓት እንደሚሆኑ ዶክተር ታምራት አብራርተዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ በበኩላችው፥ አዲስ ወግ ከፖለቲካ ግብዓትነት አኳያ ትልቅ ሚና የተጫወተ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።

በአዲስ ወግ የተንሸራሸሩ ሀሳቦች በመንግሥት በኩል ቅቡልነት አግኝተው በሪፎርሙ ተግባራዊ በመደረጋቸው፤ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ትልቅ ሀገራዊ ለውጦች እንዲመጡ አስችለዋል ብለዋል።

በልማት ድርጅቶች እና በፋይናንስ አካታችነት ሪፎርም እንዲሁም በምግብ ዋስትና እና በግብርና ምርታማነት የተገኙ ተጨባጭ ውጤቶችም ቀደም ብለው በአዲስ ወግ መድረክ መንሸራሸራቸውን ጠቅሰዋል።

በአዲስ ወግ የመደመር ትውልድ የውይይት መድረኮች በተንሸራሸሩ ሀሳቦች መነሻነት በስነ ህዝብ እና በትምህርት ፖሊሲዎች ላይ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን፤ በቱሪዝም፣ በተቋማት ግንባታ እና በሌሎችም መስኮች ጉልህ የፖሊሲ ማሻሻያዎች በደረጋቸውን እና ተግባራዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ጠቅሰዋል።

አዲስ ወግ ለፖሊሲ ማሻሻያ ሀሳቦች ግብዓቶች የተወሰዱበትና የወቅቱን ችግሮች የቃኙ ለነገም የፖሊሲ ግብዓት የሚያገለግሉ እንደሆኑ አጽንኦት ሰጥተዋል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top