"የባህር በር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት" በሚል መሪ ሀሳብ በሰላም ሚኒስቴር እና በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት የተለያዩ አካላት የተሳተፉበት አውደ ጥናት እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በአውደ ጥናቱ መክፈቻ መልዕክት ያስተላለፉት የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ከማል አብዱረሂም (ዶ/ር) ኢትየጵያ የባህር ለማግኘት እያደረገች ያለው ጥረት የሀገሪቱን ዘርፈ ብዙ ዕድገት ለማጠናከር የሚያስችል በመሆኑ ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
በተለይም የዩኒቨርሲቲ ምሁራን የኢትዮጵያን የባህር በር ጉዳይ ላይ በአግባቡ ግንዛቤ እንዲጨበጥ ጥናት ላይ የተመሠረቱ ስራዎችን በመስራት ለስኬታማነቱ ተግተው ሊሰሩ አንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያን የባህር በር ጉዳይ በማስመልከት ጥናታዊ ጽሁፎችን ያቀረቡት የአሶሳ እና የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ኢትዮጵያ ካሏት መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች አንጻር የባህር በር ጥያቄዋ ተገቢነት ያለው መሆኑን ገልጸው፤ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡
ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ መረዳት እንደሚቻለው የባህር በር ከሚፈጥረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ባሻገር ፖለቲካዊ አንድምታውና ለሰላም የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ምሁራኑ ባቀረቡት ጽሁፍ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጽያ የባህር በር አልባ በመሆኗ አየደረሰባት ያለው ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖም ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ምሁራኑ፤ ለጅቡቲ ብቻ ለባህር በር ኪራይ በየዓመቱ 2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደምታወጣም አብራርተዋል፡፡
በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በመካሄድ ላይ ባለው አውደ ጥናት የሰላም ሚኒስቴር፣ የመንግስት ኮሚውኒኬሽን ሚኒስቴር እና የለያዩ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተገኝተዋል፡፡
በጀማል አህመድ