ሎንግ በሚለው ቅፅል ስሙ የሚታወቀው በምስራቅ ጉጂ ዞን የሸኔ የሎጂስቲክስና የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ገመዳ ዱጎ ለመከላከያ ሠራዊት እጁን ሰጠ

5 Mons Ago
ሎንግ በሚለው ቅፅል ስሙ የሚታወቀው በምስራቅ ጉጂ ዞን የሸኔ የሎጂስቲክስና የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ገመዳ ዱጎ ለመከላከያ ሠራዊት እጁን ሰጠ

በምስራቅ ጉጂ እና አካባቢው ሲንቀሳቀስ በነበረው የሸኔ ቡድን ላይ ሠራዊቱ እየወሰደ በሚገኘው የተቀናጀ ወታደራዊ እርምጃ የቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች እጃቸውን እየሰጡ እንደሚገኙ የክፍለጦር ዋና አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል ገብሬ ጋሞ ገልፀዋል። 

ሠራዊቱ ሰበቦሩ እና ዳዋ በሚባሉ አካባቢዎች በጠላት ላይ በወሰደው እርምጃ ከፍተኛ ድል መቀዳጀቱን ዋና አዛዡ ገልፀው፤ የሠራዊቱን ብርቱ ክንድ መቋቋም ያቃተው የሸኔ ታጣቂ ቡድን ላይ ተፅዕኖ መፍጠር መቻሉን ገልፀዋል። 

በዚህም ሎንግ በሚለው ቅፅል ስሙ የሚታወቀው በምስራቅ ጉጂ ዞን የቡድኑ የሎጂስቲክስ እና የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ገመዳ ዱጎ ለሠራዊቱ እጁን ሰጥቷል ብለዋል። 

ሠራዊቱ አስቸጋሪና ፈታኝ በሆኑ መልክዓ ምድሮች ላይ ግዳጁን በብቃት ከመወጣቱም ባሻገር፤ የቡድኑን እኩይ ዓላማ በመበጣጠስ እና ጠላትን እፎይታ በመንሳት ተገደው እጃቸውን እንዲሰጡ እያደረገ እንደሚገኝም አብራርተዋል። 

ለሠራዊቱ እጁን የሰጠውና በጉጂ ዞን የሸኔ የሎጂስቲክስ እና የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ የነበረው ገመዳ ዱጎ (ሎንግ)፥ ዓላማ በሌለው እና ህዝብን በሚጎዳ ተግባር ላይ መሳተፉ ጥቅም እንደሌለው እና እንደማያዋጣ በማመን ለሠራዊቱ እጁን መስጠቱን ተናግሯል። 

በ1987 ዓ.ም የሽብር ቡድኑን እንደተቀላቀለ የሚናገረው የቡድኑ ከፍተኛ አመራር፥ ላለፉት በርካታ ዓመታት ህዝብን በማሰቃየትና በመዝረፍ ላይ የተሰማራው ሸኔ በሠራዊቱ በተወሰደበት እርምጃ እየተበታተነ እና አመራሩም ጭምር በሀሳብ እየተፈረካከሰ እንደሚገኝ አብራርቷል። 

ቡድኑ አሁን ላይ ህዝብን ከመዝረፍ ውጪ ምንም ዓላማ ስለሌለው እጁን መስጠቱን ገልፆ፤ በየጫካው ተበታትነው የሚገኙ የቡድኑ ታጣቂዎች ለሠራዊቱ እጃቸውን በመስጠት ወደ ሠላማዊ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ጥሪ ማቅረቡን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የማኅበራዊ ትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top