በዛሬ የፍጻሜ ጨዋታ ንስሮቹ ከፍ ብለው ይበራሉ ወይስ በዝሆኖቹ ይጨፈለቃሉ?

2 Mons Ago
በዛሬ የፍጻሜ ጨዋታ ንስሮቹ ከፍ ብለው ይበራሉ ወይስ በዝሆኖቹ ይጨፈለቃሉ?
34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ 51 ጨዋታዎችን አካናውኖ ለዛሬው የፍጻሜ ዕለት ደርሷል፡፡ በፍጻሜው ሁለቱ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራትን ያፋልማል፡፡
 
እስካሁን በተደረጉት 51 ጨዋታዎች 116 ግቦች ማለትም በያንዳንዱ ጨዋታ በአማካይ 2.27 ግቦች ተቆጥረውበታል፡፡ ይህም በ2021 በ52ቱ ጨዋታዎች ከተቆጠሩት 100 ግቦች (በያንዳንዱ ጨዋታ 1.9) የተሻለ እንደሆነ ቁጥሮች ያሳያሉ፡፡
 
ዘንድሮ የተመዘገቡትን 116 ግቦችን ለማስቆጠር 345 ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ተደርገዋል፤ ይህ ማለት እያንዳንዱ ሙከራ ወደ ግብ ቢቀየር በአማካይ 6.76 ግቦች ይቆጠሩ ነበር እንደ ማለት ነው፡፡ 33 ግብ ያልተቆጠሩባቸው ጨዋታዎች ግብ አስተናግደው ቢሆን ኖሮ የሚቆጠሩ ግቦች ከዚህ በላይ ይሆኑ እንደነበር ማሳያ ነው፡፡
 
1 ሺህ 538 ጥፋቶች ተሰርተው፣ 160 ቢጫ ካርዶች፣ 13 ቀይ ካርዶች ተመዘውበታል፡፡ 17 ፍጹም ቅጣትምቶች እና 452 የማዕዘን ምቶች በጨዋታዎቹ ላይ ተገኝተዋል፡፡
 
እንደ ግብፅ፣ ሞሮኮ፣ ሴኔጋል፣ ቱኒዚያ እና አልጄሪያ የመሳሰሉ ለዋንጫ የተገመቱ የአፍሪካ የእግር ኳስ ኃያላንን በጊዜ ከውድድር ውጪ መሆናቸው የዘንድሮውን መርሐ ግብር ልዩ ያደርገዋል።
 
ያለፉትን ሁለት የአፍሪካ ዋንጫዎች በሀገራቸው አሰልጣኞች የቀረቡ ቡድኖች የወሰዱ ሲሆን፣ የአልጄሪያው ጃሜል ቤልማዲ በ2019 ግብፅ ያዘጋጀችውን ሲያሸንፉ፤ የሴኔጋሉ አሊዩ ሲሴ ደግሞ በ2021 ካሜሩን ያዘጋጀችውን ከሴኔጋል ጋር ወስደዋል።
 
ዘንድሮ ወደዚህ ጨዋታ ከመጡ የ24ቱ ቡድኖች አሰልጣኞች መካከል ከዚህ ቀደም ዋንጫውን ወስደው የነበሩት ሦስቱ ብቻ ናቸው። እነሱም የአሁኑ የደቡብ አፍሪካ አሰልጣን ሁጎ ብሩስ እ.ኤ.አ. በ2017 ከካሜሩን ጋር፣ ጃሜል ቤልማዲ በ2019 ከአልጄሪያ ጋር፣ አሊዩ ሲሴ 2021 ከሴኔጋል ጋር አሸናፊ ሆነዋል። ከነዚህ ውስጥ ቤልማዲ እና ሲሴ በጊዜ ከውድድሩ ሲሸኙ ሁጎ ብሩስ ትላንት ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ጋር ባደረጉት ጨዋታ 3ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል፡፡
 
የ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ 7 ሚሊዮን ዶላር የሚያገኝ ሲሆን ሁለተኛ ሆኖ የሚጠናቀቀው ቡድን 7 ሚሊዮን ዶላር ወደ ካዝናው ያስገባል። ይህም በ2021 ከነበረው የ5 ሚሊዮን እና 2.5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት አድጎ የቀረበ የገንዘብ መጠን ነው፡፡
 
ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁ ቡድኖች እያንዳንዳቸው 2.5 ሚሊዮን ዶላር ያገኙ ሲሆን፣ በሩብ ፍጻሜ የተሰናበቱ አራቱ ቡድኖች እያንዳንዳቸው 1.3 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይዘው ወደ ሀገራቸው ተሸኝተዋል።
 
በዛሬው የፍጻሜ ጨዋታ በአንድ ምድብ የነበሩ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ይጋጠማሉ፡፡ በምድብ ጨዋታ ናይጄሪያ ኮትዲቯርን 1 ለ ባዶ አሸንፋ ኢኳቶሪያል ጊኒን ተከትላ ወደ ቀጣይ ዙር ያለፈች ሲሆን፤ ኮትዲቯር ደግሞ የሌሎችን ውጤት ጠብቃ ምርጥ ሦስተኛ በመሆን ነው ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈችው፡፡
ናይጄሪያ ከሁለት ዓመታት በፊት ሥራቸውን በጀመሩት ፖርቹጋላዊው ሆዜ ፔሴሮ እየተመራች ለዋንጫው ትፋለማለች። እስካሁን ሁለት ግቦች ብቻ የተቆጠሩባት መሆኗም የተከላካይ መስመሯን ጠጣርነት ያሳያል፡፡
 
በምድብ ጨዋታዎች በተከሰተው የውጤት ቀውስ ዋና አሰልጣኟን ያሰናበተችው ኮትዲቯር በጊዜያዊ አሰልጣኟ ኤመርሴ ፋኤ መሪነት ለፍጻሜው ትቀርባለች፡፡ የ40 ዓመቱ ፋኤ ኃላፊነቱን ከተረከቡ በኋላ ያደረጋቸውን ሦስት ጨዋታዎች በአሸናፊነት አጠናቋል፡፡
 
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ በፊት ባደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች ናይጀሪያ ሦስቱን በማሸነፍ የበላይነት ስትይዝ፣ ኮትዲቯር ሁለቱን አሸንፋ ቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል፡፡
 
የንስሮቹ እና የዝሆኖቹ የፍጻሜ ፍልሚያ ከ5 ሰዓት ጀምሮ አቢጃን በሚገኘው እና 60 ሺህ 12 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ባለው ኢቢምፔ ኦሎምፒክ ስታዲየም ይደረጋል፡፡
 
ጨዋታውን ታሪክ ራሱን ደግሞ ናይጄሪያ በበላይነት ታጠናቅቃለች ወይስ በሜዳቸው እና ደጋፊያቸው ፊት የሚጫወቱት ኮትዲቯሮች ያሸንፉ ይሆን? ውጤቱን ምሽት በኢቢሲ ሁሉም የማሰራጫ አማራጮች የምንመለከት ይሆናል፡፡
 
በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top