የ"ፈንዞ" ጌታ …

2 Mons Ago
የ"ፈንዞ" ጌታ …
የግዮን ወንዝ ከሚፈልቅበት ግርጌ ያለ፤ ከዓመት እስከ ዓመት ልምላሜ ደጁን የማያጣው፤ ለኑሮ ምቹ የሆነ አየር ባለቤት፤ ነጭ ጋቢ ኩታን ደራቢ፤አመስጋኝ አራሽ ህዝብ ያለበት፤በአማራ ክልል ከሚገኙ ብሔረሰቦች አንዱ፤ በቀየው የሚመረተውን ቀርቅሀ ሲያሻው ላጥር ሲፈልግ ለወንበሩ አመቻችቶ በእጁ እንጨትን የሚሸምን ህዝብ የሚገኝበት አገው ምድር።
 
ጥር ወር ሲመጣ ወገቡን ታጥቆ የዘመናት ወዳጁን አጋዡን የቤትም የውጭም ግርማውን "ፈንዞን" ይዞ አደባባይ ላይ ይታያል። ማነህ ቢባል "እኔ የ'ፈንዞ' ጌታ፣ የ'ሻሾ' ጌታ፣ አይሞሎ እንበል ጋሻ እንምታ" ብሎ ይጋብዛል።
 
ለአገው ህዝብ ፈረስ ተወዳጅ እንስሳው ነው። ከጥንት ጀምሮ እርሻውን የሚያርሰው፤ የሚወቃውም በፈረሱ ነው። ድግስ፣ሰርግ፣ለቅሶ ቢጠራ ጦርነት ቢመጣ ያለፈረሱ አይሆንለትም፤ ከእንስሳት የተመረጠ ለቤቱ ቀኝ ነው ፈረሱ።
 
የአገው ህዝብ ይህንን ቁርኝቱን ለማስታወስ ነበር በ1933 ዓ.ም በሰባት ቤት አገውፈረሰኞች ማህበር የሚመራ ታሪካዊው በዓል ብሎ ማክበር የጀመረው፤ይኸው አሁን 84ተኛ ዓመቱ ላይ ደርሷል።
 
ፈረሱን አገው ሲይዝ በፍቅር ተንከባክቦ፤የተመረጠውን መግቦ ነውና ፈረሱም ለጌታው ታዛዥ ነው። ታዲያ በየዓመቱ ጥር 23 ሲመጣ ይህ ታዛዥ ፈረስ በቀይ ጌጥ ተሽቆጥቁጦ፣የሀገሩን መለዮ ባንዲራ አንግቶ ከባለቤቱ ጋር ለሱ ክብር በተሰናዳ ድግስ ላይ ይገኛል። ሜዳው አይበቃውም ይቦርቃል በቄንጠኛ አካሄድ ትርዒቱን ያቀርባል።
 
የ"ፈንዞ ጌታ"፣ የ"ጥርኝ" ጌታ፣ የ"ቡላል" ጌታ፣የ"ታጠቅ" ጌታ… የዚያን ቀን ከፈረሱ ጋር እየተንጎማለለ በመስኩ ላይ መታየት ክብሩ ነው።
 
ይህንን ትልቅ በዓል የሚያከብረው ማህበር አሁን ላይ 65 ሺህ አባላት አሉት፤ እነዚህ አባላቱ በየወሩ መዋጮ ያዋጣሉ፣ ይመክራሉ፣ ይዘክራሉ፣ይጠያየቃሉ፤ በችግርም ይሁን በደስታ ፈረሶቻቸውን ይዘው ይገኛሉ።
 
የማህበሩ አባል ለመሆን የፈረስ ባለቤት መሆን ባይጠይቅም፤ አገው እራሱን ከፈረሱ ውጭ ማሰብ አይችልምና ብዙሀኑ ፈረስ ገዝተው አባል ይሆናሉ።
 
የማህበሩ አባል የሆነ ግለሰብ ቀን ጥሎት ወርሀዊ መዋጮ ባይከፍል፤ ችግሩን ይጠየቃል፤ ካለሳመነም ይቀጣል። አባሉ ከብቱን ንብረቱን ቤቱን በአደጋ ቢያጣ፤ መዋጮ ይደረግለታል፤ ንብረት ይተካለታል፤ በተለይ ፈረሱን በሞት ካጣ ሰጋር ፈረስ ተገዝቶ ይሰጠዋል፤ ይህ ደግሞ የአገው ባህል ነው።
 
በየዓመቱ የማህበሩ በዓል ሲከበር ሀይማኖት፣ ፆታ እና ዕድሜ ሳይገድብ ሁሉም ፈረሱን ይዞ ይሰግራል ፤ ይታያል ፤ ይዋባል ፤ ያከብራል። ታዲያ በዚህ መሀል መውደቅ፣ መሰበር፣ መነሳት ይኖራልና ወጌሻውም በቅርብ ርቀት በመሆን በዐሉን ይታደማል፣ ይጠብቃል፣ ያክማል።
 
ይህ ላለፉት 83 ዓመታት የቀጠለ፤ በአድዋ ጦርነት ከፊት የቀደመ፤ በ5 ዓመቱ የፋሽስት ቆይታ ጣሊያንን ያርበደበደው የአገው ምድር ፈረሰኞች ባህል ነው።
 
ዘንድሮም 84ተኛውን የአገው ፈረሰኞች ባህል ለማክበር ህዝቡ በጉጉት፤ ከተሞችም በድምቀት እየጠበቁ ይገኛሉ።
 
ለብዙ ዓመታት የዘለቀ የህዝብ በዓል ነውና ቅድመ ዝግጅታችንን አጠናቀናል ሲልም የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምርያ ገልጿል።
 
እኛም "እንኳ ሱኺቲፅካ ሴዛንቲ አሜትስ አዊው ፌሬስቴንስ ባልስ ዴክስ ታምፁናስ። ሽጊ ባል ያኻይምኻና" ብለናል።
 
በናርዶስ አዳነ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top