ኢትዮጵያ ሰራሿ "ፀሐይ" አውሮፕላን ወደ አገሯ ልትመለስ ነው

2 Mons Ago
ኢትዮጵያ ሰራሿ "ፀሐይ" አውሮፕላን ወደ አገሯ ልትመለስ ነው

እኤአ በ1935 በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራችው "ፀሐይ" አውሮፕላን ከጣሊያን ወደ አገሯ ልትመለስ ነው። 

"ፀሐይ" እኤአ በ1935 በጀርመናዊው ኢንጂነር እና የንጉሱ ፓይለት ሄር ሉድዊግ ዌበር ብሎም በወቅቱ በነበሩ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ትብብር በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰራች አውሮፕላን ናት። 

ስያሜዋም የቀዳማዊ ኃይለስላሴን ልጅ ልዕልት ፀሐይን ለማሰብ  የተሰጠ ነበር። 

"ፀሐይ" ባለሁለት መቀመጫ እና ሁለትዮሻዊ መቆጣጠሪያ ያላት ብሎም የባለከፍተኛ ኃይል ሞተር ባለቤት ተደርጋ የተሰራች አውሮፕላን ነበረች። 

"ፀሐይ" ኮምፓስ፣ የአብራሪ መቆጣጠሪያዎች፣ ሁለት ያለ ፍሬን ማቆሚያ የተገጠሙ የማረፊያ ሽክርክሪቶች የነበሯትም ነበረች። 

ሞተሯ ባለሰባት ሲሊንደር ዋልተር ቪነስ ሲሆን፤ የውሃ ማቀዝቀዣ ስርዓትም የነበራት የ115 የፈረስ ጉልበት ባለቤትም ነበረች። 

"ፀሐይ" ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት በኢትዮጵያ የተሰራች ብቸኛ አውሮፕላን ናት። 

"ፀሐይ" በውስን ሃብት እና ስፍራ በጊዜው የነበሩትን አናፂዎች እውቀት እና የእጅ ጥበብ በመጠቀም የተሰራች አውሮፕላን ስትሆን፤ የ1930ዎቹ የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ጥረት ማሳያ ሆና የምታገለግል ናት። 

አውሮፕላኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት ከጣሊያን መንግሥት በይፋ ተረክበዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን በተመለከተ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ብስራት፥ "ዛሬ ፀሐይ አውሮፕላንን ከጣሊያን መንግሥት በይፋ መረከባችንን የምናከብርበት ታሪካዊ ቀን በመሆኑ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ታላቅ የኩራት ቀን ነው" ብለዋል። 

ላለፈው አንድ ዓመት አውሮፕላኑን የመመለስ ሂደቱን ሲያግዙ በመቆየት ለውጤት ያበቁ የጣሊያን አቻቸው ጂኦርጂያ ሜሎኔንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመስግነዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top