"ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ የላቀ ምስጋና አቀርባለሁ" - አቶ ደመቀ መኮንን

2 Mons Ago
"ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ የላቀ ምስጋና አቀርባለሁ"  - አቶ ደመቀ መኮንን

አቶ ደመቀ መኮንን በብልፅግና ፓርቲ በተደረገላቸው የሽኝት መርሃ ግብር ላይ ንግግር አድርገዋል፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ ያስተላለፉት መልእክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ገናና እና የረዥም ዘመን ታሪክ ባለቤት የሆነችው አገረ ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ እኛ ላይ ደርሳለች። እኔም ለረዥም ዓመታት በቆየሁባቸው የፓርቲ እና የመንግስት የአመራር ቦታዎች ኢትዮጵያ ምስጢረ ብዙ መሆኗን በውል ተገንዝቢያለሁ።

በአመራር ዘመኔ ከሁሉም በላይ ትልቅ ቦታ የምሰጠው የኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የሥልጣን ቅብብሎሽ በመጠፋፋትና በፍርስራሽ ላይ ከመገንባት ወጥቶ በትውልድ ቅብብሎሽና ስልጡን አግባብ መቀጠል ሲችል ነው። ይህ በአሁኑ ዘመን እየታየ ያለ በጎ ጅምር ነው።

እያንዳንዱ ዘመን የራሱ ስኬት እና ጉድለት አለው። የቱንም ያህል ብንጣላ ታሪክን መዝለል አንችልም። ታሪክ ያው ታሪክ ነው።

የሚመዘንበትም ሁነቱ በተፈጸመበት አውድ እና ጊዜን መሠረት ተደርጎ ነው። ትልቁ ብልሀት ታሪክ ወቃሽ ከመሆን ታሪክ መስራት ነው። ሁሉም በየተራው ያለፈውን እያወገዘ ራሱን በቀጣዩ የባሰ ተወቃሽና ተጠያቂ ላለመሆን ሀገርና ትውልድ አሻጋሪ ታሪክ መስራት ይገባል።

እኔ በተሠማራሁባቸው፣ የኃላፊነት ደረጃዎች፣ አመራር በሰጠሁባቸው ጊዚያት እና ውሎዎች የተማርኩት ነገር ቢኖር ምን ያህል ፅኑ ሕዝብ እና ብርቱ አገር ያለን መሆኑን ነው። ይህን አገርና ህዝብ የሚመጥን አመራር በየደረጃው መገንባት እጅግ ተገቢ ነው።

ባሁኑ ሰዓት ያለፉትን ወረቶች በላቀ ደረጃ ለመጠቀም ጉድለቶችን እያረሙ የመጓዝን አካሄድ ለመከተል አበረታች እርምጃዎች ይታያሉ። ኢትዮጵያ እንደ ሀገርና ኢትዮጵያዊያን እንደ ህዝብ ታላላቅ አጀንዳዎችን ወጥነናል።

እንደ ህዳሴ ግድብ ያሉትን አባይን የማልማት አይነኬ የሚመስሉትን ወደ ውጤት ማብቃት፤ አዳዲስ አይነኬ መሳይ የትውልድ ጥያቄዎች (የባህር በርና ወደብ) በይፋ አጀንዳ አድርጎ በመውጣት ትልቅ የይቻላልና የስኬት ጎዳና ተጀምሯል። ለዚህ እውቅና አለመስጠት ንፉግነት ነው።

በዚህ የለውጥ ተስፋ ላይ ሆነን በውስጣችን በተለያዩ አካባቢዎች እያጋጠሙ ያሉ የሰላም እጦቶችና ፈርጀ ብዙ ጉዳቶች ሞት፣ መፈናቀል፣ ምስቅልቅል ማህበራዊ መስተጋብር በእጅጉ ልብ የሚሰብር ነው።

እነዚህን ችግሮች ህዝብን ባሳተፈ ሁኔታ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ ሁሉም ቁርጠኛ ሆኖ መንቀሳቀስ ይገባል።

ከዚህ ችግር ለመውጣት መደማመጥ፣ የሃሳብ ተግባቦት መፍጠር፣ መተማመን እና ከችግሮች በላይ የሆነ ሁነኛ መፍትሄ መሻት እጅግ አስፈላጊ ነው። ለዚህ አጀንዳ መሳካት በመንግስት መሪነት የህዝብ ባለቤትነትና የሌሎች ባለድርሻ አካላት አወንታዊ ሚና ወሳኝ ነው።

በዘመናችን ያጋጠመንን የሀገረ መንግስት ግንባታ ፈተና ለመሻገር በህዝባችን ሰፊ ተሳትፎና ባለቤትነት ተቋማትን የማጠናከር፣ ሕገ-መንግሥትን ከማሻሻል ጀምሮ ሌሎች ስብራቶችን በማረም በሁሉም መመዘኛ ለዜጎቿ የተመቸችና የበለፀገች ሀገር ለመገንባት በፅናት መረባረብ ይጠይቃል።

አሁን ባለው ተገማች ያልሆነው የአለም ጂኦ ፖለቲካ፣ የአለም አቀፍ ስርዓትና በቀጠናችን ያሉትን ተግዳሮቶች ተሻግረን ብሔራዊ ጥቅማችንን ለማስከበር ውስጣዊ አንድነታችንን ማጠናከር፣ የዜጎችን የደህንነት ስጋት ማስወገድ፣ የብሔርተኝነትና አካባቢያዊነት ችግር ፈተን ወደ አገራዊ ማማ መሻገር አለብን።

ጥበብ በተሞላበት መንገድ በጊዜ የለኝም መንፈስ ለፅኑ ሕዝባችን እና ብርቱ አገራችን የበኩላችንን ዓሻራ ለማሳረፍ ጊዜን በመቅደም ከነገ ተበድረን ጭምር ዛሬን በውጤታማነት በመጠቀም ስማችን በታሪክ ምዕራፍ ላይ በደማቅ ቀለም እዲያርፍ እንጂ በወቀሳ ዶሴ እንዲጠቀለል ዕድል መስጠት የለብንም። አዲሱ ትውልድ አዲስ ታሪክ መጻፍ አለበት!! አለብን!! ይቻላልም!!

ከአንድ ትውልድ ዕድሜ በላይ በአመራርነት ጉዞ ስኬትንም ፈተናንም በማየትና በማስተናገድ ለዚህ በቅቻለሁ። ለዚህ ላበቃኝ ፈጣሪ፣ ለቤተሰቦቼ ለመላው የስራ ባልደረቦቼ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ የላቀ ምስጋና አቀርባለሁ።

በዚህ ረጅም የአመራር ዘመን በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ላጎደልኩት ሁሉ ነገር ይቅርታ እጠይቃለሁ።

በመጨረሻም ሀገርን ለማበልፀግ በየደረጃው ለተሰማራችሁ ሁሉመልካም የስራ ጊዜ እንዲሆንላችሁ እየተመኘሁ ይህ ልዩ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ለተደረገልኝ ሽኝት አክብሮት ይስጥልኝ እላለሁ።

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!!

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top