ኃያላኑ ጡንቻቸውን የሚለካኩበት የኒውክሌር መሣሪያ

8 Mons Ago
ኃያላኑ ጡንቻቸውን የሚለካኩበት የኒውክሌር መሣሪያ

ወቅታዊ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ስምምነት ውዝግቦች

ከሁለት ሳምንት በፊት የሩሲያ ፓርላማ ከዚህ በፊት አፅድቆት የነበረውን አጠቃላይ የኒውክሌር ሙከራ ክልከላ ስምምነትን/(Comprehensive Nuclear-Test-Ban Treaty (CTBT)/ የሚሽር አዋጅ አውጥቷል። ባለፈው ሳምንት ደግሞ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ይህን በሀገራቸው ፓርላማ የፀደቀውን አዋጅ ፈርመው ሕግ እንዲሆን አድርገዋል።

ሩሲያ እ.አ.አ መስከረም 10 ቀን 1996 በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ጸድቆ እሷም ተቀብላ በምክር ቤቶቿ ካጸደቀችው ከዚህ ስምምነት ለመውጣቷ እንደ ምክንያት ያቀረበችው አሜሪካን ጨምሮ ስምንት ሀገራት ስምምነቱን በየምክር ቤቶቻቸው አለማጽደቃቸውን ነው።

የሩሲያ ዋነኛ ትኩረት ግን ከፍተኛ የኒውክሌር የጦር መሣሪያ የታጠቀችው አሜሪካ መሆኗ እዚህ ላይ ሊሰመርበት ይገባል። የዚህ በሁሉም አካባቢዎች ለሲቪልም ሆነ ለወታደራዊ ዓላማ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ፍንዳታዎችን እና ሌሎች የኑክሌር ሙከራዎችን ማድረግ የሚከለክል የባለብዙ ወገን ስምምነት መሰረዝ ከዘጠኝ ወር በፊት ሩሲያ ከሰረዘችው የሁለቱ ኃያላን የኒውክሌር ስምምነት ጋር ተደምሮ የሚፈጥረው አንድምታ ምን ሊሆን ይችላል?

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሜር ፑቲን እ.አ.አ የካቲት 21 ቀን 2023 የሀገራቸውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልከተው በቴሊቪዢን ባደረጉት ዓመታዊ ንግግራቸው፣ ሀገራቸው ከአሜሪካ ጋር ተፈራርማ ከነበረው የኒውክሌር የጦር መሣሪያ አጠቃቀም ስምምነት (New START Treaty) መውጣቷን አስታወቁ።

የሀገራቸው ከስምምነቱ መውጣት ምክንያትም አሜሪካ ራሷ ስምምነቱን መጣሷ በተለይም በኔቶ አሳብባ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎቿን ወደ አውሮፓ እያጓጓዘች መሆኗን ጠቅሰዋል።

ፑቲን ሀገራቸው ከስምምነቱ መውጣታቸውን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት “አሜሪካ በሩሲያ ላይ በምታካሂደው የውክልና ጦርነት ምክንያት ሞስኮ እ.አ.አ በ2010 በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈረመውን ስምምነት ሰርዛ ተሳትፎዋን አቋርጣለች” ብለዋል። የሀገራቸውን አቋም ሲገልጹም “ዋሽንግተን እና ኔቶ ሩሲያ በዩክሬን እንደተሸነፈች በግልጽ ባወጁበት ባሁኑ ወቅት በስምምነቱ መሰረት በኒውክሌር ጣቢያዎቿ ላይ የሚደደርግን ምርመራ ሩሲያ አትቀበልም” የሚል ነው።

እንደ National Public Radio መረጃ ፑቲን ሞስኮ ሙሉ በሙሉ ከስምምነቱ እንደማትወጣ ያረጋገጡ ሲሆን፣ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ሀገሪቱ በስምምነቱ ሥር የተቀመጡትን የጦር መሣሪያዎች ቁልፍ አጠቃቀም ጥንቃቄዎችን ታከብራለች ብሏል።

አንድ የአሜሪካ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ከፍተኛ ባለሥልጣን ሩሲያ በስምምነቱ ላይ ያላትን ተሳትፎ ማቋረጧን አጥብቀው ቢተቹም፣ ዋሽንግተን ተግባራዊነቱን ለማረጋገጥ ከሞስኮ ጋር መሥራቷን መቀጠል አለባት ብለዋል።

የአሜሪካ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ምክትል ኃላፊ የሆኑት ቦኒ ጄንኪንስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ ፎረም ላይ ባደረጉት ንግግር፣ አሜሪካ የሩሲያ ከስምምነቱ መውጣት የሚያስከትለውን ውጤት ሙሉ በሙሉ አልገመገመችም፤ ነገር ግን "አሁንም ቢሆን ሩሲያ ለስምምነቱ ተገዢ አለመሆኗን የሚያሳይ ምንም ማስረጃ አላገኘንም" ብለዋል። አክለውም፣ "ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ከሩሲያ ጋር በቅርበት ለመሥራት ዝግጁ ነን" ብለዋል።

የኒውክሌር (አቶሚክ ቦምብ) መነሻ

ኒው ሳይንቲስት (New Scientist) የተባለ ሳምንታዊ የሳይንስ መጽሔት እንዳሰፈረው፣ ለኒውክሌር ቦምብ መፈልሰፍ ምክንያት የሆነው የማንሃተን ፕሮጀክት ነው። ሂትለር በጀርመን ሥልጣን ሲይዝ ወደ እንግሊዝ የተሰደደው አይሁዳዊው ሊዮ ዢላርድ እ.አ.አ መስከረም 12 ቀን 1933 ለንደን ውስጥ ራስል አደባባይ አቅራቢያ ያለውን መንገድ ለማቋረጥ እየተጠባበቀ ሳለ ሐሳብ መጣለት፤ ይህን ሐሳብም ወደ አሜሪካዋ ማንሃተን የአቶሚክ ቦምብ ፕሮጀክት አደገ።

የማንሃተን ፕሮጀክት ነሐሴ 13 ቀን 1942 ተጀመረ። የዢላርድ መነሻ ሐሳብ የአልበርት አንስታይን E = mc2 የኢነርጂ ፎርሙላን በመጠቀም በከፍተኛ ሁኔታ ፍንዳታ የሚፈጥር አካል መፍጠር ነው። ሐሳቡ ከተጠነሰሰ ከ12 ዓመታት ገደማ በኋላ የመጀመሪያው የአቶሚክ ቦምብ ሙከራ እ.አ.አ ሐምሌ 1945 በሜክሲኮ በረሃ ውስጥ ተካሂዶ ውጤታማ ሆነ።

እ.አ.አ ነሐሴ 6 እና 9/1945 አሜሪካ በሂሮሺማ እና ናጋሳኪ የጃፓን ከተሞች ላይ ሁለት አቶሚክ ቦምቦችን ጥላ 240 ሺህ ያህል ሰዎችን ፈጀች። አሜሪካ በጃፓን ላይ ይህን እርምጃ እንድትወስድ ምክንያት የሆናት የጃፓን ንጉሣዊ አየር ኃይል ሀዋይ ሆኖሉሉ በሚገኘው በፐርል ኸርበር የአሜሪካ የባሕር ኃይል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሰንዝሮ አስደንጋጭ ጉዳት በማድረሱ ነበር።

አሜሪካ አቶሚክ ቦምብ መታጠቋን ያየችው ሶቪዬት ኅብረት በወቅቱ መሪዋ ጆሴፍ ስታሊን ጥብቅ ትዕዛዝ በኢጎር ኩርቻቶቭ አማካኝነት አርዛማስ-16 የተባለ ምሥጢራዊ ቦታ ላይ ምርምር ጀመረች። ቀደም ባሉት ዓመታት በማንሃተን ፕሮጀክት ውስጥ በሕቡዕ የተሰማሩ የሶቪየት ሰላዮች፣ በተለይም ክላውስ ፉክስ ለፕሮጀክቱ ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽ እንዳበረከተም ይነገራል።  የሶቪየት ተመራማሪዎችም ፉክስ የሰጣቸውን ዝርዝር ንድፎች በመጠቀም “ፋት ማን” የተባለ አቶሚክ ቦምብ መሥራት ጀመሩ ። በምዕራባውያን “ጆይ-1” ተብሎ የተሰየመው ይህ ቦምብ እ.አ.አ ነሐሴ 29 ቀን 1949 ካዛኪስታን ውስጥ በሴሚፓላቲንስክ የተደረገውን ሙከራ በስኬት አለፈ።

በሁለቱ ኃያላን ሀገራት የነበረው ስምምነት ምንድን ነው?

አዲሱ ስምምነት (The New START) የሚባለው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ባራክ ኦባማ እና የወቅቱ የሩሲያው አቻቸው ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ እ.አ.አ በ2010 የፈረሙት ሲሆን፣ ሀገራቱ የሚታጠቁት የኒውክሌር አረር ብዛት ከ1 ሺህ 550፣ እንዲሁም አህጉር አቋራጭ ሚሳኤሎች ከ700 እንዳይበልጥ ይደነግጋል። ሁለቱ ሀገራት ከሚስማሙባቸው በላይ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች እንዳይኖራቸውም ይገድባል። የስምምነቱን ተፈጻሚነት ለመገምገም መሣሪያዎቹ ባሉበት ቦታ በመገኘት የመስክ ምርመራ ማድረግን ይፈቅዳል። ከሁለቱ ሀገራት የተውጣጡ አባላት ያሉበት እና ገለልተኛ አካላት የተካተቱበት የምርመራ ቡድን እንሚቋቋም እና የተመረጡ ሚዲያዎችም እንደሚሳተፉበት ያስቀምጣል።

እንደ አሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከ2020 ወዲህ ምርመራው የተቋረጠ ሲሆን፣ ካለፈው ኅዳር ጀምሮ ወደ ውይይት ለመመለስ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ሩሲያ በአንፃሩ ከዩክሬን ጦርነት ጋር ተያይዞ ከምዕራባውያን ጫና እየተደረገብኝ ነው በማለት ስምምነቱ ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል ስትገልጽ ቆይታለች።

ቀዝቃዛው ጦርነት

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እ.አ.አ 1947 እስከ 1991 የቆየው ውጥረት ቀዝቃዛው ጦርነት ይባላል። ውጥረቱ የተፈጠረው በሁለቱ የኒውክሌር ቦምብ ባላቤቶች አሜሪካ እና ሶቪየት ኅብረት መካከል ነበር። ቀዝቃዛው ጦርነት ያተኮረው በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በፕሮፓጋንዳ ግንባር ላይ ሲሆን ሁሉንም ችግሮች ለመፍታት ግን የጦር መሣሪያ ፉክክርን እንደ መጨረሻ አማራጭ የተመለከተ ነበረ። ውጥረቱ እያደገ መጥቶ አሜሪካ አጋሮቿን አስተባብራ ኔቶን በመመሥረት በአውሮፓ የጦር ሰፈሮቿን ማቋቋም ስትጀምር ሶቭየት ኅብረት በበኩሏ ኩባ ውስጥ በምሥጢር የኒውክሌር ግንባታ ጀመረች።

ውጥረቱ ቀጥሎ እ.አ.አ በጥቅምት 1962 ለ13 ቀናት የቆየው የመጨረሻ የኩባ ሚሳኤል ቀውስ ላይ ደረሰ። በነዚህ ጊዜያት አሜሪካ በጣሊያን እና በቱርክ የኑክሊየር ሚሳኤሎችን አጓጉዛ ለጥቃት ስትዘጋጅ፣ በኩባ የነበረውን የሶቪየት ኅብረት ምሥጢራዊ የኑውክሌር ሚሳኤሎች ዝግጅት አታውቅም ነበር።

እንደ የአሜሪካው “The Office of Historian” የመረጃ ምንጭ፣ አደገኛነቱን የተረዳችው አሜሪካ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሮበርት ኬኔዲ አማካኝነት በአሜሪካ ከሶቭየት ኅብረት አምባሳደር አናቶሊ ዶብሪኒን ጋር በምሥጢር ተገናኝተው ሀገራቸው የጁፒተርን ሚሳኤል ከቱርክ ለማውጣት ዝግጁ መሆናቸውን አሳውቀው፣ በአፋጣኝ ይህን እንደምታደርግም ቃል ገቡ። በማግሥቱ ጥቅምት 28 ቀን ጠዋት የሶቭየት ኅብረቱ ፕሬዚዳንት ኒክታ ክሩስቼቭ ሀገራቸው ሚሳኤሎቿን ከኩባ እንደምታነሣ በይፋ መግለጫ ሰጡ።

ቀዝቃዛው ጦርነት በዚሁ ሲጠናቀቅ ሁለቱ ሀገራትም ዳግም ተመሳሳይ ውጥረት እንዳይፈጠር የኒውክሌር ስምምነቶችን ተፈራረሙ።

ለመሆኑ ከላይ የተጠቀሰው ስምምነት ለምን አዲስ ተባለ?

እ.አ.አ በ1985 የሶቭየት ፕሬዚዳንት ሚካኤል ጎርባቾቭ እና የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬገን በጋራ "በኒውክሌር ጦርነትን ማሸነፍ ስለማይቻል በፍፁም መሣሪያውን መጠቀም አያስፈልግም" ሲሉ ትልቅ እመርታ ያሳየ የተባለለት ስምምነት ላይ ደረሱ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሁለቱም ሀገሮች መሪዎች ይህን ሐሳብ ሲያቀነቅኑ ኖረዋል። በ2010 አዳዲስ ሐሳቦችን ጨምረው ስምምነቱን አድሰውት ነበር።

እ.አ.አ በጥር 2022 የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ የቻይና፣ የፈረንሳይ እና ሁሉም የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ባለቤቶች እና የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላት በጉዳዩ ላይ ተወያዩ። ይሁን እንጂ ይህ ውይይት ከደረገ በኋላ በተጀመረው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ውስጥ ሌሎች ሀገሮች ከገቡ እና ህልውናዋ አደጋ ውስጥ ከገባ ኒውክሌር እንደምትጠቀም ሩሲያ አስጠነቀቀች።

Gorbachev and Reagan: the capitalist and communist who helped end the cold  war | Mikhail Gorbachev | The Guardian

ዓለም አቀፍ የኒውክሌር ሕግ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኒውክሌር የጦር መሣሪያዎች ቅነሳ ስምምነት አንቀጽ ስድስት “ኒውክሌር የታጠቁም ሆነ ያልታጠቁ መንግሥታት የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ፉክክር በማቆም የኒውክሌር የጦር መሣሪያ ቅነሳን በተመለከተ በሚወሰዱ እርምጃዎች ላይ ለተደረሰው ስምምነት የመገዛት ግዴታ አለባቸው” ይላል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ግን በ1970 ሥራ ላይ የዋለው እና በ191 ሀገሮች የተፈረመው ይህ የመንግሥታቱ ድርጅት ሰነድ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ቅነሳ ስምምነት ምርመራዎችንም የሚጨምር ቢሆንም ሁለቱ ግዙፍ ኒውክሌር ባለቤቶች ከተፈራረሙት ስምምነት ጋር አይጣጣምም።

የኒውክሌር ጦር መሣሪያን በይፋ የታጠቁ ሀገራት እና አቅማቸው

ዓለም ከኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች ነጻ መሆን አለባት ብሎ እንቅስቃሴ እያደረገ ያለው ‘ICAN’ የተባለ ደርጅት ባወጣው መረጃ  ሩሲያ፣ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ፓኪስታን፣ ሕንድ፣ እስራኤል እና ሰሜን ኮሪያ በይፋ ኒውክሌር የታጠቁ ሀገራት መሆናቸውን ጠቁሟል። አነዚህ ዘጠኝ ሀገራት በጥቅሉ 12 ሺህ 700 የኒውክሌር የጦር መሣሪያዎች ያሏቸው ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 9 ሺህ 400 የሚሆኑት በወታደራዊ ክምችት ውስጥ ይገኛሉ።

ሩሲያ እና አሜሪካ በቅደም ተከተል 5 ሺህ 998 እና 5 ሺህ 428 የኒውክሌር አረሮችን የታጠቁ ሲሆን፣ ይህም ከጠቅላላው 90 ከመቶውን ይሸፍናል።

እንደ ‘ICAN’ ሪፖርት፣ አንድ የኒውክሌር የጦር መሣሪያ አረር በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ይገድላል፤ ዘላቂ እና አውዳሚ የሆነ ሰብዓዊ እና የአካባቢ ጉዳትም ያስከትላል። አሁን ካሉት ኒውክሌር ቦምቦች አንዱ ኒው ዮርክን በሚያክል ግዛት ላይ ቢፈነዳ 600 ሺህ ያህል ሰዎችን ይቀጥፋል።

ሁኔታው ወደ የት ያመራ ይሆን?

በካሊፎርኒያ በሚገኘው የጄምስ ማርቲን የዩሬዥያ ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ሣራ ቢድጉድ እንዳሉት "አሁን ያለውን ሁኔታ ስመለከት ወደ ኒውክሌር ጦርነት እያመራን ነው ብለን ልንከራከር እንችላለን፣ ነገር ግን እዚህ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ፑቲን ሩሲያ ከስምምነቱ ማግለላቸውን ሲናገሩ ምን ማለት እንደፈለጉ ማወቁ ወሳኝ ይሆናል" ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም "ፑቲን ሩሲያ ከስምምነቱ ትወጣለች ማለታቸው በሺህ የሚቆጠሩ ተጨማሪ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን አዘዋውራለሁ ማለታቸው አይደለም፤ ይልቁንስ ምርመራውን ላለማስቀጠል ሕጋዊ ምክንያት አለኝ ማለታቸው ይመስለኛል፤ የሆነው ሆኖ ይህ የሩሲያ እርምጃ በወደፊቱ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር እና አላስፈላጊ የጦር መሣሪያ ፉክክሮችን ለማለዘብ በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል" ብለዋል።

የዋሽንግተን ዓለም አቀፍ የኒውክሌር ፖሊሲ ፕሮግራም ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ሊን ሩስተን በበኩላቸው፣ "አሁን በኒውክሌር የጦር መሣሪያ ውድድር ላይ አይደለንም፤ ይሁን እንጂ በቅርቡ ሁኔታዎች መቀየራቸው አይቀሬ ነው፤ ምክንያቱም የአሜሪካ እና የሩሲያ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች ስምምነት የመጨረሻው ስለሆነ ነው፤ እናም አሁን ነገሮች በፍጥነት ውጥረት ውስጥ እንደገቡ ግልጽ ነው፤ ላለፉት ሦስት ዓመታት በሁለቱ ሀገራት መካከል በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት ውይይት አለመደረጉ መጪውን ጊዜ አሳሳቢ አድርጎታል" ብለዋል።

ዓለም ላይ የኒውክሌር ጦርነት ቢከሰት ምን ይፈጠራል?

በማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ተቋም ውስጥ የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ማክስ ቴግማርክ ታይም መጽሔት ላይ በጻፉት ሀተታ እንደገለጹት፣ የኑክሌር ጦርነት ቢከሰት ፍንዳታዎችን፣ የኤሌክትሮማግኔቲክ ንዝረት እንዲሁም ከፍተኛ ብክለት የሚፈጥር ጥቁር የካርቦን ጭስ ይፈጠራል። እነዚህ ወደ ላይ ከፍ ብለው በዓለም ዙሪያ ሲሰራጩ ዓለምን ከፍተኛ ሙቀት እና ቃጠሎ ውስጥ ሊከቱ ይችላሉ።

90 በመቶ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ የታጠቁት አሜሪካ እና ሩሲያ ጦርነቱን ቢጀምሩ አንደኛው ወገን የኑክሌር ሚሳይሎችን ሲተኮስ ሌላኛው ወገን ደግሞ የመልስ ምት ለመስጠት መተኮሱ አይቀሬ ነው። በዚህም መሰረት አሜሪካ ከኖርዌይ በስተምዕራብ ከሚገኘው የጦር ሰፈሯ ከሚገኙት ሰርጓጅ መርከቦቿ ላይ የሚተኮሱ ባሊስቲክ ሚሳይሎች ሩሲያን ከ10 ደቂቃ ገደማ በኋላ መምታት ይጀምራሉ፤ ሩሲያ ደግሞ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ከሰሜን ካናዳ አቅጣጫ አሜሪካን መምታት ተጀምራለች።

የመጀመሪያው ተኩስ ከፍተኛ ቮልቶችን መፍጠር የሚችሉ በአስር ሺህዎች የሚቆጠር የኤሌክትሮ ማግኔቲክ ንዝረትን ይፈጥራል። በታቃራኒውም ያለው ኃይል የአጸፋ እርምጃ ሲወስድ ቀውሱ እየተባባሰ ይሄዳል። በየሀገራቱ ያሉ ትላልቅ ከተሞች እና የጦር ሰፈሮች የጥቃቶቹ ዒላማ ይሆናሉ። እያንዳንዱ የሚተኮሰው የኒውክሌር ሚሳኤል እሳተ ገሞራ በመፍጠር የፀሐይን ያህል ሙቀት ያለው የእሳት ቃጠሎ ይፈጥራል፤ ቀጥሎም የራዲዮአክቲቭ ጨረር ደመናን ይሸፍናል። እነዚህ ኃይለኛ ፍንዳታዎች ሕንጻዎችን የሚያፈራርሱ ሲሆን በአቅራቢያቸው የሚኖሩ ሰዎችን በመግደል ዓለምን ምስቅልቅል ውስጥ የሚከት ኃይለኛ ማዕበል ያስከትላሉ። እናም የኒውክሌር ጦርነት ቢጀመር በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በሩሲያ እና በቻይና ውስጥ የሚኖሩ 99 በመቶ ጨምሮ ከ5 ቢሊዮን በላይ የዓለም ሕዝቦች በረሃብ ሊሞቱ ይችላሉ።

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top