አደራን ለበላ እምነት ላጎደለ፣ ሕጋችን ምን አለ?

6 Mons Ago
አደራን ለበላ እምነት ላጎደለ፣ ሕጋችን ምን አለ?

"አየሽ አንቺ እማማ አየሽ አንቺ እናት ዓለም፣

ቃል የእምነት ዕዳ እንጂ የእናት የአባት እኮ አይደለም።"

ከሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ ቴያትር ቃለ-ተውኔት ላይ የተቀነጨበ ስንኝ ነው። ስለመታመንና ዕምነት ሳስብ እነኚህ የታላቁ ባለቅኔያችን ስንኞች በምናቤ ውስጥ ይመላለሱብኛል።

ሕጉ እምነትን ለማስጠበቅ ምን ደንግጓል?

ሌሎች ሰዎች ላይ የምንጥለው እምነት አንዳንዴ ሊያደርስብን ከሚችለው ጉዳት የሚጠብቀን ማን ነው? ፈጣሪ፣ ህሊና፣ ሕግ ወይስ የእኛ ጠንቃቃነት? መልሱ ከሰው ሰው ይለያያል። ለመሆኑ በወንጀል ሕጋችን እምነት ማጉደል ምንድን ነው? ምን ዓይነት ኃላፊነትስ ያስከትላል?

የወንጀል ሕጋችን በአንቀፅ 662 ላይ ዓላማ አድርጎ የተነሳው ንብረትን ወይም በገንዘብ የሚተመኑ መብቶቻችንን ለመጠበቅ እንደሆነ ይነግረናል። ያመንነው ሲከዳ ንብረት ወይም ገንዘባችን ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ነው እምነትን ማጉደል ያስቀጣል ሲል ሕጉ የደነገገው።

እምነት ማጉደል በወንጀል ሕጋችን በአንቀፅ 675(1) አገላለፅ መሰረት ለራስ ወይም ለሌላ ሰው የማይገባ ጥቅም ለማስገኘት ከሌላ ሰው በአደራ ወይም ለተወሰነ አገልግሎት የተቀበለውን ዋጋ ያለውን ነገር ወይም ጥሬ ገንዘብ መመለስ አለመቻል ነው። አንድ ሰው እምነት አጎደለ የሚባለውም ድርጊቱን የፈፀመው አላግባብ ራሱን ወይም ሌላውን ለመጥቀም አስቦ ከሆነ ነው። ከዚህ ሀሳብ ውጭ በሆነ ሁኔታ የተነሳ አደራውን ማክበር ወይም ንብረቱን መመለስ ሳይችል ቢቀር እምነት አጉድሏል ሊባል አይችልም።

ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው የማይገባውን ጥቅም ለማስገኘት ማሰቡ ብቻ ሳይሆን የተሰጠውን ንብረት ወይም ገንዘብ ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው መውሰድ፣ ማስወሰድ፣ መሰወር ወይም ጥቅም ላይ የማዋል ድርጊቶችን የመፈፀም ድርጊት ነው እምነት የማጉደል ወንጀልን የሚመሰረተው።

በተጨማሪም ማንም ሰው ለመግዛት፣ ለመሸጥ ወይም ለተወሰነ ስራ የተሰጠውን ንብረት ወይም ገንዘብ በተባለው መሰረት ፈፅሞ ያገኘው ገንዘብ ወይም ዋጋ ያለው ዕቃ በእምነት የተሰጠው እንጂ የራሱ ስላልሆነ ሲጠየቅ የመመለስ ግዴታ አለበት። ይህን ካልፈፀመ በእምነት ማጉደል ወንጀል ያስጠይቀዋል።

በእምነት ወይም በአደራ የሰጠሁህን መልስ? የሚል ጥያቄ ሲመጣ ንብረቱን ወይም በገንዘቡን መመለስ ወይም በተጣለበት እምነት መሰረት ለተገቢው አገልግሎት መዋሉን ማስረዳቱ ግድ ይላል። ይህን ማድረግ ያልቻለ ሰው በወንጀል ሕጋችን በአንቀፅ 675(3) መሰረት ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው የማይገባ ጥቅም ለማስገኘት አደራ እንደበላ ወይም እምነት እንዳጎደለ ይቆጠራል።

አሁን ደግሞ የካሳ ተሰማ አስገምጋሚ ድምፅ በክራሩ ታጅቦ እንዲህ ሲያንጎራጉር በምናባዊው ጆሮዬ ይሰማኛል።

"የአምባሰል ማር ቆራጭ ይወጣል በገመድ

አደራ ቢሰጡት ይበላል ወይ ዘመድ?"

አደራ ተበላ እምነትም ጎደለ እናስ?

የወንጀል ሕጋችን በአንቀፅ 675(1) ላይ እምነት ማጉደሉ የተፈፀመው በግለሰብ ላይ ከሆነ እንደ ነገሩ ከባድነት እምነት አጉዳዩን በቀላል እስራት ወይም ከ5 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስር እንደሚያስቀጣው ይደነግጋል።

እምነት ማጉደል በመንግስት ወይም በሕዝባዊ ድርጅቶች ባለስልጣናት፣ በሕዝብ ባላደራ ወይም ተመራጭ ሲፈፀም ደግሞ የተበላው የሕዝብ አደራ የተካደውም የሕዝብ እምነት ነውና ቅጣቱ ከብዶ ከ5 እስከ 25 ዓመት ፅኑ እስራትና እስከ መቶ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል።

በተለይ በሕግ የሞግዚትነት፣ የንብረት አጣሪነት፣ አስተዳዳሪነት ስልጣን የተሰጠው ሰው፤ የሕግ ወይም የገንዘብ አማካሪ፣ ጠበቃ፣ ወኪል፤ ለራሱ ወይም ለንግድ ማህበር፣ ለባንክ፣ ለሌላ ድርጅት ገንዘብ የሚሰበስብ ሰው፤ በተጣለበት ኃላፊነት በእጁ በገባ ሰነድ ላይ አስመስሎ በመፈረም እምነት ካጎደለ የመንግስት ባለስልጣን ባይሆንም ከ 1 እስከ 15 ዓመት ፅኑ እስር ይቀጣል።

የውል ግዴታን አለመወጣት እምነት ማጉደል ነው?

አቶ ጀማል የትራንስፖርት ድርጅት ነበረው። መስከረም 6 ቀን 2003 ዓ.ም ከተበዳይ ላይ ግምቱ 180,000.00 ብር የሆነ አንድ ካርቶን እሽግ ዕቃ ከአዲስ አበባ ጎንደር ለማድረስ ተስማምቶ የማጓጓዣ ዋጋውን ብር 150 ይቀበላል። ጀማል ባለበትም የጀማል ሰራተኞች ዕቃውን ይረከባሉ። ነገር ግን ጀማል በገባው የማጓጓዝ ስምምነት መሰረት ዕቃውን ለተቀባዩ ሊያደርስ ወይም ያላደረሰበትን ምክንያት ሊያስረዳ ስላልቻለ በተበዳዩ አቤቱታ አቅራቢነት የእምነት ማጉደል የወንጀል ክስ ተመሰረተበት።

የወንጀል ክሱ የቀረበለት የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤትም ጀማልን የእምነት ማጉደል ወንጀል ፈፅመሀል ሲል ፈረደበት። ከፍተኛው ፍ/ቤትም ጀማል ያቀረበውን ይግባኝ ባለመቀበል ፍርዱን አፀናው። በመሆኑም ጀማል በእምነት ማጉደል ወንጀል ጥፋተኛ በመባሌ የሕግ ስህተት ተፈፅሟል ሲል ለፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት የሰበር አቤቱታ አቀረበ።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም በመ⁄ቁ 74530 ሰኔ 24 ቀን 2004 ዓ.ም በዋለው ችሎት ጀማል በተለመደው የሥራ ሁኔታው አጓጉዞ የተወሰነ ስፍራ ለማድረስ የገባውን የማጓጓዝ  ውል ባለመወጣቱ የእምነት ማጉደል የወንጀል ክስ ቀርቦበት በስር ፍ⁄ቤት የተፈረደበትን የእስር ቅጣት በመሻር ውሳኔ ሰጠ። ሰበር ሰሚ ችሎቱ በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜም አንድ ሰው በገባው ውል መሰረት ግዴታውን ሳይወጣ ቢቀር በፍትሐብሔር ክስ የውል ግዴታውን ባለመወጣቱ ያጎደለውን እንዲተካ ወይም ተመጣጣኝ ካሳ እንዲከፍል ከመጠየቅ በቀር በእምነት ማጉደል ወንጀል ሊጠየቅ አይገባም ብሏል።

ከሕግ ተጠያቂነት ባሻገር የመታመን ዋጋው ስንት ነው?

ባለቅኔው ፀጋዬ ገ/መድህን እንዳለው ቃል የእምነት ዕዳ ነው። ከሕግም ሆነ ከማንም በፊት የሚጠብቀው ህሊናችን ነው። በመሆኑም ሕሊናችንን በማክበር የተጣለብንን እምነት መጠበቅ አለብን። ከህሊና ተግሳፅ አልፎ እምነትን ማጉደል ደግሞ ከላይ ባነሳነው አግባብ የሕግ ተጠያቂነትም ያስከትላል።

ከላይ ያነሳነው የእምነት ማጉደል የሕግ ተጠያቂነት እንዳለ ሆኖ እምነት ማጉደል ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዳይተማመኑ ያደርጋል። የተበላብን አደራ የተካደብን እምነት የሚያሳጣን ገንዘብ ወይም ቁሳዊ ነገር ብቻ ሳይሆን ሰዎችን የማመን አቅማችንንም ጭምር ነው። ሰዎች ላይ የምንጥለው እምነትስ  እምነት በማጉደላቸው ሲሸረሸር በምን ይመለስ ይሆን? በዚህች አጭር ግጥም እናሳርግ፡-

"የካዱኝ በሙሉ ሀቄን የበሉብኝ

ቀን ሲሞላላቸው ሰፍረው መለሱልኝ።

ፊቴ እንደቀጨመ

አፌ አመሰገነ።

"ምን ቀረህ?" ይሉኛል ገፅታዬን ያዩ

ስፍር የማይለካው ጉድለቴን ያልለዩ

የወሰዱት ሁሉ ተቆጥሮ ሲመጣ

እምነቴ ግን ቀርቷል ከልቤ እንደወጣ።"


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top