የገንዘብ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የ2015 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም እና የሦስት ዓመት የልማት እና ኢንቨስትመንት ዕቅድ ላይ ግምገማ ተካሄዷል።
በግምገማው ላይ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሺዴ፣ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት እና የተቋማት አመራሮች ተገኝተዋል።
በቀረበው የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት የገንዘብ ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ የመንግሥት የልማት ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎችን መነሻ ያደረገ እና በጥናት ላይ የተመሠረተ የፊስካል ፖሊሲ አዘጋጅቶ ሲተገብር መቆየቱ ተገልጿል።
ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት፣ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እንዲሁም የመንግሥት የበጀት ጉድለት መጠን እና የእዳ ጫና እንዲቀንስ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸው ተመላክቷል።
የመንግሥት ገቢን ለማሳደግ የኢኮኖሚ ዕድገቱን መነሻ ያደረጉ የተለያዩ የታክስ ክፍያ አማራጮችን እየተተገበሩ መሆኑን በሪፖርቱ ላይ መመላከቱን የገንዘብ ሚኒስቴር ገልጿል።
በበጀት ዓመቱ ከልማት አጋሮች ሊገኝ የሚችለውን የውጭ ሀብት ለማሰባሰብ በተለይም የእርዳታ እና የብድር ግኝትና ፍሰት የማሳደግ፣ የመልሶ ማቋቋም እና ግንባታ ፕሮግራም የመተግበር የተለያዩ የኢኮኖሚ ትብብር እና አጋርነትን የማጠናከር ሥራዎች መከናወናቸውም ነው የተጠቀሰው።
በጥሬ ገንዘብ ዕቅድ መሠረት ክፍያ የመፈጸም፣ ነቀፌታ ያለበትን የኦዲት ግኝት የመቀነስ፣ የተሻሻለ የመንግሥት ፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓት የመዘርጋት እና የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ክፍያን እና ግዢን እንዲስፋፉ የማድረግ ተግባራትም ከሥራዎቹ መካከል ይገኙበታል።
የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) የገንዘብ ሚኒስቴር የሚያወጣቸው ደንቦች እና መመሪያዎች የሌሎች ተቋማትን ግብዓትን በማካተት መሆን እንዳለባቸው እና ይሄም አጠቃላይ አፈጻጸምን ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የታክስ ማሻሻያዎች ውጤታማነትን ለማረጋገጥ አሠራርን በቋሚነት መፈተሸ አስፈላጊ መሆኑንም አመልክተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሺዴ በበኩላቸው፣ በበጀት ዓመቱ ከነበረው ጫና አንፃር የፊስካል አስተዳደሩ ጥሩ አፈጻጸም እንዳሳየ ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ በእዳ አከፋፈል፣ በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ በማቋቋም እና በፕሮጀክቶች አፈጻጸም የተከናወኑ ዐበይት ተግባራት ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ከ2016 እስከ 2018 በጀት ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው የሦስት ዓመት የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ የ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ማስተግበሪያ ነው።
ዕቅዱ የኢትዮጵያን ልማት እና ዕድገት በማፋጠን ረገድ ወሳኝ አስተዋጽኦ እንዳለው እንደታመነበትም ሚኒስቴሩ ገልጿል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።