እየተባባሰ የመጣው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊታረም እንደሚገባው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አሳሰበ

9 Mons Ago 699
እየተባባሰ የመጣው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊታረም እንደሚገባው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አሳሰበ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ በተመለከተ ከኢቲቪ ዳጉ ፕሮግራም ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በሀገራችን ባለው የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ የተሻሻሉ ጉዳዮች ቢኖሩም እየተባባሱ የመጡ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በስፋት ይስተዋላሉ።

በአንድ በኩል፥ በኢትዮጵያ ባለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታ ላይ የተሻሻሉ ጉዳዮች አሉ። ለአብነትም መንግሥትም ኮሚሽኑ የሚያስፈልጋቸውን ከማሟላት ጀምሮ በሥራው ላይ ጣልቃ ላለመግባት ያደረገው ጥረት ለሰብዓዊ መብት መጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የነበረው ጦርነት በሰላም እና በውይይት መጠናቀቁ፣ የደቡብ ክልል ህዝበ ውሳኔዎች በሰላማዊ መንገድ መካሄዳቸው፣ የማረሚያ ቤቶች አያያዞች መሻሻላቸው፣ ያልተገባ እርምጃ በሚወስዱ የመንግሥት የፀጥታ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃዎች መወሰድ መጀመራቸው ከታዩት መሻሻሎች መካከል መሆናቸውን ነው ዶክተር ዳንኤል የገለጹት። 

ይሁንና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አሁንም በስፋት ይስተዋላሉ ብለዋል።

በበርካታ አካባቢዎች በትጥቅ በታገዙ ግጭቶች ምክንያት በዜጎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመር አንድ ማሳያ እንደሆነ ነው የገለፁት።

በርካታ ሰዎች ለዘፈቀደ እስር እየተዳረጉ መሆናቸውም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን ገልጸው፣ ከህግ ውጭ መታሰር ብቻ ሳይሆን የታሰሩ ሰዎች ተገቢ ላልሆነ አያያዝ መጋለጣቸውም በስፋት ይስተዋላል ብለዋል።

በዚህ ሂደትም ብዙዎች ተገቢ ላልሆነ ድብደባ እና እንግልት ተጋልጠዋል ብለዋል። ይህ ዓይነቱ አካሄድ ከለውጡ ማግስት በነበሩት ዓመታት ተሻሽሎ የነበረ ቢሆንም በዚህ ዓመት ግን እየተባባሰ መሄዱን በምርመራችን አረጋግጠናል ብለዋል።

አንዳንድ ሰዎችን የመሰወር ጉዳይም በስፋት እየተስተዋለ ያለ አደገኛ ልምምድ ነው ብለዋል።

የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በወንጀል ጠርጥረናል የሚሏቸውን ሰዎች መደበኛውን የህግ ሂደት ተከትሎ አለማሰር፣ አለመመርመር፣ አለማጣራት ብቻ ሳይሆን ሰዎቹ ያሉበት ቦታ እስከማይታወቅ ድረስ አስገድደው እንደሚሰውሩ ተናግረዋል።

በዚህ ሁኔታ የተሰወሩ ሰዎችን ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥ አግኝተን አነጋግረናቸዋል ያሉት ኮሚሽነር ዳንኤል፣ ባነጋገርናቸው ጊዜ በተሰወሩበት ወቅት ድብደባ እና እንግልት እንደደረሰባቸው ተረድተናል፤ እስካሁንም ተሰውረው የቀሩ ሰዎች አሉ ብለዋል።

የሚዲያ አካላት ላይ የሚፈጸም እስር እና እንግልትም እየተለመደ መምጣቱን አስታውሰው፤ ከሚዲያ ጋር ተያይዞ ወንጀል ተፈጽሟል ተብሎ በታሰበበት ወቅት ቅድመ ክስ ምርመራ ሳያስፈልግ ክስ መመስረት እንደሚቻል የተቀመጠ ግልጽ ህግ እየተጣሰ ነው ብለዋል። 

ከልማት ጋር ተያይዞ የሰዎች መፈናቀል፣ የተፈናቀሉ ሰዎች የተሟላ ሰብአዊ እርዳታ አለማግኘት እና ዘላቂ የሆነ መፍትሔ አለመሰጠት ሊታረሙ የሚገባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሆኑም ተናግረዋል።

በህይወት የመኖር መብት፣ ከቦታ ቦታ በነጻነት የመንቀሳቀስ መብቶች አሳሳቢ ሁኔታ ወስጥ እየገቡ መሆናቸውንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። 

በታጠቁ ቡድኖች የሚደርሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ መንግሥት የህዝቡን ሰላም እና ደህነነት የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበት ጠቁመው፤ እነዚህን አካላት ሰበብ በማድረግ የሚፈጸሙ ጥሰቶችን ማስቆም እና በመንግሥት የፀጥታ አካላት የሚፈጸሙ እንግልቶችንም ማረም አለበት ብለዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኮሚሽኑ ለሚሰራቸው ሥራዎች ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርግላቸውም ነው ኮሚሽነር ዳንኤል የገለጹት።

ነገር ግን የሚሰጡ ምክረ ሀሳቦች የማይተገበሩባቸው ሁኔታዎች አሁንም ተግዳሮት እየሆኑ ስለመጡ መንግሥት ውስጡን መርምሮ ወጥ የሆነ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) አሳስበዋል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top