የአፍሪካ ኅብረት 60ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ከግንቦት 17 ቀን ጀምሮ ይከበራል፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

11 Mons Ago
የአፍሪካ ኅብረት 60ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ከግንቦት 17 ቀን ጀምሮ ይከበራል፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት 60ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ከግንቦት 17 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ዓመት እንደሚከበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በዓሉ የአህጉሪቱን አንድነት በሚያጠናክሩ የተለያዩ መርሐ-ግብሮች እንደሚከበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ አስታውቀዋል።

የኅብረቱ አባል ሀገራት በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች በየሀገራቸው እንደሚያከብሩም ጠቁመዋል።

በበዓሉ ፓን አፍሪከኒዝምን ለማስረፅ የተደረጉ ጥረቶች እና የቅኝ አገዛዝ ቀንበርን ለመስበር የተደረጉ ትግሎች እንደሚዘከሩ እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት በ2063 ለማሳካት የያዘቻቸው ግቦች /አጀንዳ 2063/ እንደሚወሱበት ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በዓሉን የምታከብረው የኅብረቱን ዓላማ ለማሳካት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን በማጉላት እና የአዲስ አበባን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ለማፅናት በሚያስችል ሁኔታ እንደሆነ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል፣ ኢትዮጵያ ከላቲን አሜሪካ እና መካከለኛ እስያ ሀገራት ጋር ያላትን የግንኙነት አድማስ ለማስፋት ውጤታማ ሥራ እየሠራች መሆኑንም አምባሳደር መለስ ዓለም ጠቁመዋል።

በዚህም ከኮሎምቢያ እና ፓኪስታን ጋር ያላት የፖለቲካ ግንኙነት ዘርፈ-ብዙ የትብብር መስኮችን ማካተት የሚያስችል ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ መደረጉን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የኮሎምቢያ ምክትል ፕሬዚዳንት ፍራንሲያ ኤሊና ማርኬዝ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር በሁለትዮሽ ገዳዮች ዘሪያ ፍሬያማ ውይይት እንዳደረጉም አምባሳደር መለስ ገልጸዋል።

ምክትል ፕሬዚዳንቷ በዛሬው ዕለትም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ተገናኝተው በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የተመራ ኢትዮጵያ ልዑክ ባሳለፍነው ሳምንት በፓኪስታን ቆይታ ማድረጉም ተጠቅሷል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል በንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ ከፋች የሆኑ ዲፕሎማሲያዊ ተግባራት እንደተፈጸሙ ነው አምባሳደሩ ያስታወቁት።

በወቅታዊ የሱዳን ቀውስ ከ19 ሺህ በላይ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ የተገለጸ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያውያን ባሻገር ወደ ሀገራችን እየገቡ ያሉት ሱዳናውያን፣ ኤርትራውያን፣ ደቡብ ሱዳናውያን እና የሌሎች ሀገራት ዜጎች ጭምር መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top