የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 7 ነጥብ 5 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ እንደሚችል አመላካች ውጤቶች ተመዝግበዋል - ፕላንና ልማት ሚኒስቴር

11 Mons Ago
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 7 ነጥብ 5 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ እንደሚችል አመላካች ውጤቶች ተመዝግበዋል - ፕላንና ልማት ሚኒስቴር

ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ 7 ነጥብ 5 በመቶ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማስመዝገብ የያዘችውን ዕቅድ ለማሳካት አመላካች ውጤቶች መገኘታቸውን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባደረገው 19ኛ መደበኛ ስብሰባ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወር እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ፣ የተቋማቸውን የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርቡ በማክሮ ኢኮኖሚና ሌሎች ሀገራዊ የልማት ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራትን ዘርዝረዋል።

የ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ በተተገበረባቸው ባለፉት ሦስት ዓመታት ያጋጠሙ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎችን በመቋቋም የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት በማደግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

መንግሥት ያደረጋቸው ኢንቨስትመንቶችና ፖሊሲ ማሻሻያዎች ለተገኘው ውጤት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጋቸውንም ነው ያብራሩት።

ሚኒስትሯ የ2015 የመጀመሪያና ሁለተኛ ሩብ ዓመት በማክሮ ኢኮኖሚ በተለይም በግብርና፣ ኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፍ የተመዘገቡ የምጣኔ ኃብት እድገቶች መኖራቸውን አንስተዋል።

በዚህም በ2015 በጀት ዓመት 7 ነጥብ 5 በመቶ እድገት ለማስመዝገብ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት አመላካች ውጤቶች መኖራቸውን ነው የጠቀሱት።

በማምረቻው ዘርፍ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተከናወኑ ተግባራት፣ በአገልግሎት ዘርፍ የታየው መነቃቃት እቅዱን ለማሳካት ያግዛሉ ብለዋል።

የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ከተያዘው እቅድ አኳያ 70 በመቶ መፈጸም የተቻለ ሲሆን ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ22 በመቶ እድገት ማሳየቱን ተናግረዋል።

ይህም የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት አመላካች ውጤት ሲሆን በሪሚታንስ፣ በፋይናንስና ሌሎች ዘርፎች የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን ገልጸዋል።

ሚኒስትሯ፣ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት የማክሮ ኢኮኖሚ ፈተና መሆኑን በመለየት በትኩረት ለመስራት አቅጣጫ መያዙን ገልጸዋል።

የ10 ዓመት የልማት ዕቅዱን የሦስት ዓመታት አፈጻጸም መነሻ በማድረግ እና የልማትና ኢንቨስትመንት አፈጻጸምን በመገምገም የሶስት ዓመት የልማት እቅድና የኢንቨስትመንት ፕላን መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

በዚህም መሰረት የልማት ዕቅዱ ከእያንዳንዱ ዘርፍ የልማት መርሃ ግብርና ፕሮጀክት ጋር በተናበበ መልኩ እንዲዘጋጅ እንዲናበብ መመሪያ መዘጋጀቱን ጨምረዋል።

ሪፖርቱን መነሻ በማድረግ አስተያየትና ጥያቄ ከምክር ቤት አባላት ቀርቦ ምላሽና ማብራሪያ መሰጠቱን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ሪፖርቱ በገመገመበት ወቅት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የልማት ዕቅድን እንደ ሀገር ወጥ ለማድረግ አንድ እቅድ አንድ ሪፖርት አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስቧል።

የፕላን በጀት እና ፋይናንስ ጉዳች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ ሪፖርቱን ከተደመጠ በኋላ በሰጡት ማጠቃለያ፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደሀገር የልማት እቅዶቹን ወጥ ለማድረግ በሁሉም የመንግስት መስሪያ ቤቶች  ክልሎችን ጨምሮ እስከታች ድረስ እንዲወርድ አንድ እቅድ አንድ ሪፖርት በሚል የተዘረጋው አሰራር ቀጣይነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top