በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ላይ ሊደረጉ የሚገቡ ማሻሻያዎች ላይ የተደረገው ጥናት ይፋ ሆነ

9 Mons Ago
በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ላይ ሊደረጉ የሚገቡ ማሻሻያዎች ላይ የተደረገው ጥናት ይፋ ሆነ

የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ላይ ሊደረጉ የሚገቡ ማሻሻያዎች ላይ ያደረገውን ጥናት ይፋ አድርጓል።

የጥናቱ ትኩረት ሁሉም የሕገ-መንግሥቱ አንቀፆች ላይ ሳይሆን ብሔር ነክ በሆኑ ድንጋጌዎች ላይ መሆኑ ተገልጿል።

ኢንስቲትዩቱ ጥናቱን ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አቅርቦ ውይይት እየተካሄደበት ይገኛል።

አሁን ያለው ሕገ-መንግሥት ላለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ምንም ማሻሻያ ሳይደረግበት መቆየቱ በውይይቱ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ላለፉት ሁለት ዓመታት አከራካሪ በሆኑ የሕገ-መንግሥቱ አንቀፆች በተለይም ብሔር ነክ በሆኑ ድንጋጌዎች ላይ ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎች የማሻሻያ ጥናት ማድረጉን ገልጿል።

በጥናቱም በ2000 ዓ.ም በሕዝብ እና ቤቶች ቆጠራ ከተዘረዘሩት 83 ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መካከል 41 የሚሆኑት በስልታዊ የዘፈቀደ ዘዴ (systematic random sampling) ተመርጠዋል።

በዚህም መሠረት የሕገ-መንግሥቱ መግቢያ ላይ ያሉ የተወሰኑ ሐሳቦች፣ የብሔር ብሔረሰቦች ሉዓላዊነት አንቀፅ 8፣ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ፣ ብሔራዊ አርማ፣ ብሔርን መሠረት ያደረገው አስተዳደራዊ ወሰን፣ መገንጠልን የሚደነግገው አንቀፅ 39፣ የፖለቲካ ፓርቲን በብሔር ማደራጀት እና የአዲስ አበባ አስተዳደርን በተመለከተ መሻሻል እንዳለባቸው ሕዝቡ ፍላጎት እንዳለው ተመላክቷል።

የኢፌዴሪ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በመድረኩ ባቀረቡት የመነሻ ጥናታዊ ጽሑፍ፣ ሕገ-መንግሥቱ ከተረቀቀበት ጊዜ አንሥቶ ክርክር እየተነሣበት እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን በበኩላቸው፣ ሁሉም የሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌዎች በተለያየ መንገድ የሚሻሻሉበትን ሁኔታ አስቀምጠዋል።

በመድረኩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ዘሃራ ዑመድን ጨምሮ የፖሊሲ ባለሙያዎች፣ የሰብአዊ መብት ተቋማት ኃላፊዎች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በወይንሸት ደጀኔ


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top