የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ ክልል በጊዜያዊነት ያቆሙትን ሰብዓዊ ርዳታ ለማስጀመር እና ተጠያቂነትን ለማስፈን የምርመራ ሥራ ተጀመረ

11 Mons Ago
የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ ክልል በጊዜያዊነት ያቆሙትን ሰብዓዊ ርዳታ ለማስጀመር እና ተጠያቂነትን ለማስፈን የምርመራ ሥራ ተጀመረ

የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ ክልል “የሰብዓዊ ድጋፍ ስርጭት አቅጣጫ ስቷል" በሚል በጊዜያዊነት ያቆሙትን የርዳታ ስርጭት ለማስጀመር እና ተጠያቂነትን ለማስፈን የምርመራ ሥራ መጀመሩን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር ሺፈራው ተክለማርያም ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ባልተገደበ ሁኔታ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በትግራይ ክልል 5.2 ሚሊዮን፣ በአማራ ክልል 2.4 ሚሊዮን በአፋር ክልል ደግሞ 750 ሺህ አካባቢ ዜጎች ርዳታ እየቀረበላቸው መሆኑን አንስተዋል።

ሆኖም በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ርዳታን ተደራሽ እያደረጉ የሚገኙት የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም የሰብአዊ ድጋፍ ስርጭቱ አቅጣጫውን በመሳት ለሌላ ዓላማ እየዋለ ነው በሚል ድጋፉን በጊዜያዊነት ማቆማቸውን ማሳወቃቸውን ተናግረዋል።

ኮሚሽነር ሺፈራው የትግራይ ክልል አብዛኛው አካባቢ በጦርነት ቀጣና ውስጥ የቆየ በመሆኑ ሰፊ የሰብአዊ ድጋፍ የሚደረግበት መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም ምክንያት በእያንዳንዱ ቦታ ያለውን የርዳታ ተደራሽነትና ስርጭት ለመከታተልና ለማረም የማይቻልባቸው ሁኔታዎች ስለሚኖሩ ርዳታውን ላልተፈለገ ዓላማ የማዋል ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ይገመታል ነው ያሉት።

ድጋፉን በዋናነት የሚያቀርበው የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት እና ስርጭቱን የሚያከናውኑት የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና ሌሎች በቅንጅት የሚሰሩ አካላት ድጋፉ አቅጣጫውን የሳተበት ሁኔታ እስኪጣራ ድረስ ርዳታ በማቆም እርምት እንዲወሰድ ውይይት እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም ተጠያቂዎችን የመለየት እና በቀጣይ ሰብዓዊ ድጋፉ ለትክክለኛ ተረጂዎች ብቻ እንዲደርስ የሚያስችል ጠንካራ አሰራር የሚዘረጋበትን መንገድ የማመቻቸት ሥራ እየተሰራ መሆኑን በመጠቆም።

ችግሩ የተነሳው መንግስት በሚያደርገው የሰብዓዊ ድጋፍ ሳይሆን በዓለም አቀፍ የረድኤት ተቋማት የርዳታ ስርጭት ሂደት መሆኑን በማንሳት መንግስት ከተቋማቱ ጋር በመነጋገር የማጣራት ሥራዎች እንዲከናወኑ በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽንም ርዳታዎች ለትክክለኛ ተረጂዎች እንዲደርሱ ከርዳታ አቅራቢዎችና አሰራጮች ጋር የመሥራትና ተረጂዎችን ለይቶ የማቅረብ ሥራ እንደሚያከናውን ተናግረዋል።

ጉድለት ሲፈጠርም ተጠያቂነት እንዲሰፍንና በየደረጃው ያለው አመራር ርብርብ እንዲያደርግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ኮሚሽነር ሺፈራው አክለውም ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት እና በሰብዓዊ ድጋፍ ስርጭቱ ሚና ካላቸው አካላት ጋር በጉዳዩ ላይ መነጋገራቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የማጣራት ሥራ እያከናወነ እና እርምቶችን እየወሰደ መሆኑን እንዳሳወቀ ጠቅሰው፤ በቀጣይም ተጠያቂነትን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል ብለዋል።

የሰብአዊ ድጋፍ የሚያደርጉና የሚያሰራጩ ተቋማትም የማጣራት ሥራው በፍጥነት ተከናውኖ ስርጭቱን መልሰው እንዲጀምሩና ዳግም ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር አብረው እንደሚሰሩ መግባባት ላይ መደረሱንም ገልጸዋል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top