በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በሀገራዊ ምክክር ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ

11 Mons Ago
በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በሀገራዊ ምክክር ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ

በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በሀገራዊ ምክክር ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።

ኮሚሽኑ እንደገለጸው፣ በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ የፖለቲካ እና የሃሳብ መሪዎች እንዲሁም የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልዩነት እና አለመግባባት ይታያል።

ይህንን ልዩነት እና አለመግባባት መፍታትና ሀገራዊ መግባባት ላይ መድረስ አስፈላጊ በመሆኑ፣ እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አካታች ሀገራዊ ምክክሮችን በማካሄድ የተሻለ ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት፣ በሂደትም የመተማመንን እና ተቀራርቦ የመሥራት ባህልን ለማጎልበት እንዲቻል ገለልተኛ የሆነ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 ተቋቁሟል።

በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት ስትራቴጂክ እቅድ ነድፎ የዝግጅትና ቅድመ ዝግጅት ስራዎችን፣ የልየታ መስፈርት እና የአመራረጥ ሂደት መመሪያዎች ዝግጅትን አጠናቆ ወደ ሂደት ምዕራፍ የተሸጋገረበት ወቅት ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።

ስለሆነም በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ይህንን ታሪካዊ አጋጣሚ ተጠቅመው በሀገሪቱ የወደ ፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ተብሎ በሚጠበቀው ሀገራዊ ምክክር ላይ በንቃት እንዲሳተፉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጥሪውን አቅርቧል።

በዚህም መሰረት ኮሚሽኑ በቅርቡ በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር የበይነ መረብ ስብሰባ ለማድረግ ያቀደ መሆኑን ገልፆ የስብሰባውን ቀንና ሰዓት (በየሚኖሩበት ሀገር ሰዓት አቆጣጠር) በዝርዝር በቅርብ እንደሚያሳውቅ የምክክር ኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top