በአማራ ክልል በመገንባት ላይ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች 75ቱ ተጠናቅቀዋል፡- የክልሉ ትምህርት ቢሮ

9 Days Ago
በአማራ ክልል በመገንባት ላይ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች 75ቱ ተጠናቅቀዋል፡- የክልሉ ትምህርት ቢሮ
በአማራ ክልል በመገንባት ላይ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 75 የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መጠናቀቃቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።
 
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ መኳንንት አደመ፤ የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
 
በተለይ በመልሶ መቋቋም ጽህፈት ቤትና በክልሉ መንግስት በተመደበ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት በመገንባት ላይ ካሉ 50 የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 42ቱ ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸውን አመልክተዋል።
 
እንዲሁም በትምህርት ሚኒስቴር ድጋፍ እየተገነቡ ካሉ 45 የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 33ቱ መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።
 
በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ያለውን የክፍል ጥበት ችግር ለማቃለል የተገነቡ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች እንዳሉም ተጠቅሷል።
 
የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶቹ ከመማሪያ ክፍሎች በተጨማሪ የአስተዳደር፣ የቤተ ሙከራ፣ የቤተ መፃህፍትና የአይሲቲ ህንፃዎችና ክፍሎችን አካተው መገንባታቸውን ተናግረዋል።
 
በግንባታ ላይ የሚገኙ ቀሪዎቹ 20 የ1ኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በበጀት ዓመቱ ውስጥ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
 
ትምህርት ቤቶቹ በቀጣይ ዓመት አገልግሎት እንዲሰጡም ቢሮው 25 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት መድቦ የተማሪ መቀመጫ ወንበሮችን የማሟላት ስራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
 
እንዲሁም የኮምፒዩተርና ሌሎች ለመማር ማስተማሩ ስራ የሚያግዙ ግብዓቶችን በቀጣይ ዓመት የማሟላት ስራ እንደሚከናወንም አብራርተዋል።
 
ትምህርት ቤቶቹ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ በሁለት ፈረቃ ከ80 ሺህ ያላነሱ ተማሪዎችን ተቀብለው እንደሚያስተናግዱም መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top