ኤጂ ዋይ የተሰኘ የገበታ ጨው የሚያመርት ኩባንያ በሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ በመግባት የገበታ ጨው ምርት ላይ ለመስራት ከኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር ስምምነት ፈፅሟል።
ኩባንያው 2000 ካሬ ሜትር የለማ መሬት በመረከብ እና የራሱን ማቀነባበሪያ በመገንባት ስራ የሚጀምር ሲሆን ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ የኢንቨስትመንት ካፒታልም ያስመዘገበ ነው ተብሏል።
ኩባንያው በሙሉ አቅሙ ስራ ሲጀምር ከ350 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥርም ተገልጿል።
አሁን ላይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ በተለይም በዱቄት ወተት ምርትና ተያያዥ በሆኑ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፎች ገብተው ኢንቨስት ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶችን እያስተናገደ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።
ሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በ2 ሺ ሄክታር መሬት ላይ የተገነባ ሲሆን፤ 8 የማምረቻ ሼዶች የተገነቡለት እና ለጅቡቲ ወደብ ቅርበት ያለው ግዙፍ የኢንቨስትመንት ማዕከል ነው።