የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ስትራቴጂክ አጋርነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

11 Mons Ago
የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ስትራቴጂክ አጋርነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እያከናወነች ላለው ተግባር ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጿል።
 
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ሕብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር እያከናወነ ያለውን ተግባር አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያና የአውሮፓ ሕብረት ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸውና ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጎልበት ስትራቴጂክ ስምምነት በማድረግ እየሰሩ እንደሚገኙም አምባሳደር ሮላንድ ገልጸዋል።
27ቱ የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሚያዝያ 16/2015 ዓ.ም በሕብረቱ የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት ሊቀ-መንበርነት ባደረጉት ስብሰባ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር አዲስ መሰረታዊ መደምደሚያዎችን በሙሉ ድምጽ ማጽደቃቸውን አስታውሰዋል።
ይህ ውሳኔ በአውሮፓ ሕብረትና በኢትዮጵያ መካከል ባለው አጋርነት ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባህር ለአውሮፓ ቁልፍ ስትራቴጂካዊ አጋር ናት ያሉት አምባሳደሩ የአውሮፓ ሕብረት ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አመልክተዋል።
ይህም ሕብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ፋይዳው የጎላ መሆኑን ነው የተናገሩት።
የአውሮፓ ሕብረት በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ስትራቴጂክ አጋርነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማምጣት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በሰላም ስምምነቱ መሰረት እየተደረገ ያለው ሰብአዊ ድጋፍና ሌሎች ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውንና በሽግግር ፍትሕ መሰረት ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ፣ የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም በማምጣት የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለመፍጠር የተጀመረውን ጥረት እንደሚደግፍም ገልጸዋል።
ሕብረቱ በኢትዮጵያ መደበኛ የረዥም አመት የልማት መርሐ-ግብሩን እንደገና ለመጀመር ዝግጁ እንደሆነም ገልጸዋል።
 

ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top