የሀገራችን የፖለቲካ ተዋናያን ከሕገ ወጥ እና መርሕ አልባ እንቅስቃሴ ሊቆጠቡ ይገባል!፦ ብልጽግና ፓርቲ

1 Yr Ago
የሀገራችን የፖለቲካ ተዋናያን ከሕገ ወጥ እና መርሕ አልባ እንቅስቃሴ ሊቆጠቡ ይገባል!፦ ብልጽግና ፓርቲ
የሀገሪቱ የፖለቲካ ተዋናያን ከሕገ ወጥ እና መርሕ አልባ እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ የብልጽግና ፓርቲ ጠየቀ።
ፓርቲው ያወጣው ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፦
የብልጽግና ፓርቲ የሁሉም አቋሞቹ እና ተግባሩ መነሻ እና መድረሻ የኢትዮጵያ ኅልውና፣ ታላቅነት፣ ብልጽግና እና የሕዝቦቿ ሰላም ብቻ ነው።
በዚህ የማይናወጥ ሀገራዊ እና ሕዝባዊ መሠረት ላይ ቆመን ለመላ የሀገራችን ሕዝቦች የጋራ ደጀን፣ መከታ፣ ክንድ እና የማይታጠፍ አለኝታ የሆነ ሀገራዊ ሠራዊት ለመገንባት ሕገ-መንግሥቱን መሠረት ያደረገ ጥረቶች ማድረግ ከጀመርን ውለን አድረናል።
በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ቅስቀሳ ወቅትም የክልሎችን ልዩ ኃይል በሕገ መንግሥቱ መሠረት መልሰን እንደምናደራጅ አቋማችን ለሕዝብ ግልጽ ማድረጋችን ይታወሳል።
ስለሆነም አሁን ላይ ለብዥታ እና ተገቢውን መስመር ለሳተ የትርጉም አንድምታ የተጋለጠው ልዩ ኃይሎቻችንን መልሶ የማደራጀት እንቅስቃሴም አንዳንዶች በሚያሳዝን ሁኔታ አጣምመው እንደሚለፍፉት እንግዳ ደራሽ የሆነ የቶሎ ቶሎ ቤት ዓይነት ውሳኔ ሳይሆን በብዙ ጥናት፣ በጥልቅ ውይይት፣ በሰከነ ንግግር እና በጋራ መግባባት የተደረሰበት ውሳኔ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ከሕዝባችንም የክልል ልዩ ኃይሎች ሕገ መንግሥቱን መሠረት ባደረገ እና የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት በተሻለ መልኩ በሚያስጠብቅ አኳሃን መልሶ የማደራጀት ሥራ መሠራት እንዳለበት በተለያየ መልኩ ለመንግሥት እና ለፓርቲያችን ሲገልጽ ቆይቷል።
በመሆኑም ውሳኔው የሕዝቡን ፍላጎት ከግምት ውስጥ ያስገባ እና ሕገ-መንግሥታዊ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል። በሕገ-መንግሥታችን ላይ በማያሻማ መልኩ እንደተመለከተው ሀገርን እና ሕዝብን ከየትኛውም ጥቃት እና ጠላት የሚከላከል ሀገራዊ ኃይል የመገንባት ኃላፊነት እና ሥልጣን የፌዴራል መንግሥቱ ብቻ እንደሆነ በግልጽ ተመልክቷል።
የክልል መንግሥታትም የክልላቸውን ሰላም እና ፀጥታ የሚያስጠብቅ ክልላዊ ፖሊስ አደራጅተው እንደሚመሩ በሕገ-መንግሥቱ ተደንግጓል።
በዚህም መሠረት የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና የማደራጀት አስፈላጊነት ልክ ያልነበረን ጉዳይ ልክ የማድረግ ውሳኔ እና ጥረት እንጂ ሌላ ምንም አመክንዮ እንደሌለው በውል ሊታወቅ ይገባል።
አንዳንድ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና መሪዎቻቸው እንዲሁም ማኅበራዊ አንቂዎች ነን የሚሉ ግለሰቦች ጉዳዩን አንድን ክልል ብቻ ትጥቅ የማስፈታት ጉዳይ አድርገው የሚያቀርቡበት እና ጉዳዩን ለመግለጽ የሚጠቀሙባቸው “ማክሰም፣ ማጠፍ፣ ማፍረስ፣ መበተን…” ወዘተ የሚሉት አገላለጾች ምንጫቸው - ከየት እና ምርጫቸው - እንዴት ሆኑ የሚለውን መተንተን ለዚህ አውድ ፋይዳው ብዙ ባይሆንም ግባቸው ግን ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ እና ሕዝብን ለማሳሳት በመሞከር ጊዜያዊ ቅቡልነት ለማግኘት የመጣር ፍላጎት እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል።
ስለሆነም ከዚህ ሀገርን ዋጋ ከሚያስከፍል ሕገ ወጥ እና መርሕ አልባ እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ ፓርቲያችን ያሳስባል።
ፓርቲያችን በጽኑ መግለጽ የሚፈልገው ዋና ጉዳይ ልዩ ኃይልን ትጥቅ የማስፈታት ሳይሆን የተሻለ የማስታጠቅ፤ የመበተን ሳይሆን በጠንካራ መሠረት ላይ የማደራጀት ሥራ ላይ የመሆናችንን የማያሻማ እውነት ነው።
የሁሉም ክልል ልዩ ኃይሎች በብዙ ሀገራዊ ፈተናዎቻችን እና ድሎቻችን ውስጥ መቼም ሊደበዝዝ የማይችል ደማቅ አሻራ እንዳላቸው ፓርቲያችን በጽኑ ያምናል። በምንም ስለማይተመነው እና በነፍሳቸው ተወራርደው ስለሰጡት አገልግሎትም በተለየ አክብሮት እና ፍቅር ያመሰግናሉ።
የልዩ ኃይሎቻችን በመከላከያ፣ ፌዴራል ፖሊስ እና የክልል ፖሊስ መዋቅሮች ውስጥ ተደራጅተው ሀገርን እና ሕዝብን ማገልገል ለመላው የሀገራችን ሕዝቦች የሚኖረው አስተዋጽኦ እጅጉን ሰፊ እና መሠረታዊ ለውጥ የሚያስገኝ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።
ልዩ ኃይሎቻችንን እስከዛሬ ስትሰጡት ከነበረው አገልግሎት በተሻለ አደረጃጀት፣ ትጥቅ እና ወታደራዊ ብቃት እንድታገለግሉ አስተማማኝ ዕድል የሚያጎናጽፋቸው በመሆኑ ሕግ እና ሥርዓትን በጠበቀ አኳሃን ለውሳኔው ተግባራዊነት የበኩላቸሁን እንድትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ይህ ውሳኔ በአማራ ክልል ላይ ብቻ የተወሰነ ውሳኔ አድርገው ለማቅረብ የሚጋጋጡ ዘገር ነቅናቂ ግጭት ናፋቂ ኃይሎች የሚነዙት መርዛማ መረጃ ፍጹም ሐሰት እንደሆነ ፓርቲያችን በአጽንኦት ማሳወቅ ይፈልጋል፤ ውሳኔው ሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ተነጋግረው የተወሰነ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን በተመሳሳይ የጊዜ መስመር በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የሚተገበር መሆኑን አበክሮ ያስታውቃል።
የክልል ልዩ ኃይሎች ሕገ-መንግሥታዊ በሆኑት የፀጥታ መዋቅሮች ገብተው እንዲያገለግሉ መደረግ እንዳለበት ከብልጽግና እኩል (አንዳንዴም በላይ) ሐሳብ ሲያነሱ እና ሲሞግቱ የነበሩ ፓርቲዎች እና አመራሮችም ጭምር ዛሬ ላይ “ከስጋው ጾማለሁ ከመረቁ ስጡኝ” አይነት መግለጫ ለማውጣት መጋጋጣቸው ፓርቲያችንን እጅጉን አሳዝኖታል።
ሆኖም ግን ብልጽግና ፓርቲ በተግዳሮቶች ውስጥም ቢሆን ከሕዝባችን እና ከሁሉም የልዩ ኃይል አመራሮቻች እና አባላት ጋር በስክነት በመወያየት እና የተፈጠረውን የተግባቦት ክፍተት በመሙላት ለሀገር እና ለሕዝብ ዘላቂ ሰላም በሚበጀው ጎዳና መጓዙን ይቀጥላል።
በዚህ አጋጣሚም ሻማ እንዲሸጥላቸው ጨለማ የሚናፍቁ እና የሚጠብቁ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና መሪዎቻቸው ነገሮችን ከማባባስ እና ሞትን ለመጥመቅ - ግጭት ከመጠንሰስ እንዲቆጠቡ በአጽንኦት ለማሳሰብ እንወዳለን።
“እውነት እና ንጋት እያደረ ይጠራል” እንደሚባለው ውሳኔው ነገ ከነገ ወድያ በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ተግባራዊ ሆኖ በታሰበው መሠረት ተፈጻሚ ሲሆን ለሚታይ ግልጽ ውሳኔ ተገቢ ያልሆነ ዋጋ በመክፈል ሰላማችን እንዳይደፈርስ መላው የአማራ ሕዝብ እና የልዩ ኃይል አባሎቻችን ነገሮችን በሰከነ መልኩ እንዲያዩ እና ለዚህ ሀገርን እና ሕዝብን ለሚጠቅም ቀና ውሳኔ ቀና ምላሽ እንዲሰጡ በአክብሮት እንጠይቃለን።
ኅብረ ብሔራዊ ክንዳችን - ለሁለንተናዊ ሰላማችን!
ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት

ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top