በናይጄሪያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የገዢው ፓርቲ እጩ ቦላ ቲኑቡ አሸነፉ

1 Yr Ago
በናይጄሪያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የገዢው ፓርቲ እጩ ቦላ ቲኑቡ አሸነፉ
የናይጄሪያን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የገዢው ፓርቲ እጩ ቦላ ቲኑቡ አሸናፊ መሆናቸው ታወጀ።
የ70 ዓመቱ አዛውንት ከተሰጡት ድምፆች 36 በመቶ የሚሆነውን ማግኘታቸውን ይፋዊ የምርጫ ውጤቶች አሳይተዋል።
ዋነኛ ተቀናቃኞቻቸው አቲኩ አቡበከር 29 በመቶ እንዲሁም የሌበር ፓርቲ እጩ ፒተር ኦቢ 25 በመቶ ድምጽ አግኝተዋል።
የምርጫ ውጤቱ ይፋ ከመደረጉ በፊት ሦስት ፓርቲዎች ምርጫው የተጨበረበረ ነው በማለት ዳግም ምርጫ ይካሄድ ሲሉ ከምርጫው ራሳቸውን አግልለዋል።
ዋነኛ ተቃዋሚዎቹ ፒፕልስ ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ፒዲፒ) እና ሌበር ፓርቲ አዲሱ የኤሌክትሮኒክ የመራጮች ሥርዓት ላይ ግልጽነት የጎደለው ሁኔታ አይተናል ካሉ በኋላ የምርጫ ውጤት ከሚነገርበት አዳራሽ ለቅቀው ወጥተው ነበር።
በናይጄሪያ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ የመራጮችን ማንነት ለመለየት ጥቅም ላይ ሲውል ይህ የመጀመሪያው ነው።
የናይጄሪያ የምርጫ ኮሚሽን ግን የእነዚህን የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ቅሬታ ውድቅ አድርጓል።
ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ቲኑቡ ናይጄሪያ ካፈራቻቸው ባለጸጋ ፖለቲከኞች መካከል አንዱ ሲሆኑ የሌጎስ ግዛት አስተዳዳሪም ነበሩ።
ቲኑቡ የትውልድ አካባቢያቸው በሆነው ደቡብ ምዕራብ ናይጄሪያ በሚገኙ ግዛቶች አሸናፊ ሆነዋል።
ቲኑቡ ለሁለት የሥልጣን ዘመናት አገሪቱን ሲመሩ ከቆዩት ፕሬዚዳንት ሞሐመዱ ቡሃሪ የሚረከቧት የምጣኔ ሃብት እድገት የተቀዛቀዘባት፣ የሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር የጨመረባት እና የጸጥታ ችግር ያለባትን ናይጄሪያ ነው።
ይህ ምርጫ በናይጄሪያ ወታደራዊ አገዛዝ እአአ 1999 ካበቃ በኋላ ከፍተኛ ፉክክር ታይቶበታል መባሉን ቢቢሲ ዘግቧል።

ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top