ኢትዮጵያ በችግር ውስጥ አልፋም ጭምር ስኬታማ ሥራዎችን እና ለውጦችን ማስመዝገቧ እንዳስደነቃቸው የአፍሪካ አገራት መሪዎች መመስከራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ግንኙነት እና ፖሊሲ አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአፍሪካ ኅብረት ጎን ለጎን ከተለያዩ አገራት መሪዎች ጋር መምከራቸውን የተናገሩት አማካሪ ሚኒስትሩ፣ መሪዎች የጠበቁት የተዳከመች እና የተጎዳች ኢትዮጵያን ቢሆንም የገጠማቸው ግን በተቃራኒው ነው ብለዋል።
በተለይም በቴክኖሎጂ የዘመኑ ተቋማትን መመልከታቸው እና ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል እያደረገች ያለችው ጥረት እንዳስደነቃቸው ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በበኩላቸው፣ የኅብረቱ ጉባኤ በሰላም መጠናቀቅ ኢትዮጵያ ላይ ሲነዛ የነበረውን የተሳሳተ መረጃ ውድቅ ያደረገ እና አገሪቱ ያለምንም እንከን ትላልቅ ሁነቶችን ጭምር ለማዘጋጀት ያላትን አቅም ያሳየችበት ነው ብለዋል።
ጉባኤው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመጠናቀቁ የተሠራው የቅንጅት ሥራ ከፍተኛውን ሚና መውሰዱን ያሳወቁት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄጄራል መላኩ ፈንታ ደግሞ ኢትዮጵያ ለሌሎች አገራት ተሞክሮ መሆን የሚችል ሥራ መሥራቷን አሳውቀዋል።