ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተለያዩ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተወያዩ

1 Yr Ago 445
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተለያዩ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተወያዩ

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተለያዩ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተወያይተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ውይይቱን ያደረጉት እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ኅብረት 42ኛው የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ጎን ለጎን ነው። 

ውይይቱ የተካሄደውም ከጋቦን፣ ከጋምቢያ፣ ከማላዊ፣ ከቱኒዝያና ከሊቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ነው።  

ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለሰ ዓለም፥ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በወቅታዊ የኢትዮጵያ ሰላምና የልማት እንቅስቃሴ ላይ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ገለጻ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል። 

በዚህም ኢትዮጵያ ለሰላም ትልቅ ቦታ እንዳላት በመጠቆም የሰላም ሥምምነቱን ተግባራዊ በማድረግ በኩል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን በተመለከተ ገለጻ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።  

በመልሶ ግንባታና ማቋቋም እንዲሁም ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ስለመሆኑ ማብራሪያ መስጠታቸውንም ነው ያነሱት።  

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹም ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል በማመስገን ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ተናግረዋል።  

በተለይም ደግሞ በቱሪዝም፣ በአየር ትራንስፖርትና በሌሎች ዘርፎች ላይ በትብብር መሥራት የሚቻልባቸው የጋራ ጉዳዮች መኖራቸውን ሚኒስትሮቹ አንስተዋል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ጥንካሬ የአገራቱ ጥንካሬ እንደሆነ መጥቀሳቸውንና የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን መፍታት እንደሚቻል ኢትዮጵያ እንደ ምሳሌ የምትወሰድ አገር መሆኗን መጥቀሳቸውን ገልጸዋል።  

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በትናንትናው ዕለትም ከተለያዩ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር መወያየታቸው ይታወሳል። 

ሁለተኛ ቀኑን የያዘው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ ዛሬ ማምሻውን ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top