የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻ የልማት ፕሮጀክት አስጀምረዋል።
የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክቱ በጣልያን መንግስት የገንዘብ ድጋፍ የሚሰራ ሲሆን፣ የከተማዋን ገጽታ በማስዋብ የሚቀይር መሆኑ ተገልጿል።
የ2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የወንዝ ዳር ልማት በአዲስ አበባ ከጣልያን ኤምባሲ እስከ ጀርመን ኤምባሲ ባለው የቀበና ወንዝ ላይ የሚከናወን መሆኑ ታውቋል።
የጣልያን መንግስት ለዚሁ ፕሮጀክት የ5 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፤ የልማት ስራው የወንዙን ንጽህና የማስጠበቅ እንዲሁም ዳርቻዎቹን በማስዋብ የመዝናኛ ስፍራ የማድረግ ዓላማ እንዳለው ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ በ3 የግንባታ ደረጃ በ23 ወራት ተገንብቶ የሚጠናቀቅ መሆኑም በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፕሮጀክቱን በይፋ በማስጀመር ግንባታው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና ክትትል እናደርጋለን ብለዋል።
የጣልያን መንግስት በብዙ የልማት ስራዎች እየደገፈ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀበና ወንዝ ላይ ለሚከናወነው የወንዝ ዳር ፕሮጀክት ላደረገው ድጋፍም አመስግነዋል።
በቀበና ወንዝ ላይ የሚከናወነው የልማት ስራ አዲስ አበባን የማስዋብ ፕሮጀክት አንዱ አካል መሆኑን ጠቅሰው ለፕሮጀክቱ ግንባታ ስኬት ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ሁሉ እገዛ እንዲያደርግ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ የጣልያን አምባሳደር አጉስቲኖ ፓሌሴ፥ ኢትዮጵያና ጣልያን የረጅም ጊዜ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያላቸው አገራት መሆናቸውን አስታውሰዋል።
የጣልያን መንግስት በስራ ፈጠራ እንዲሁም በተለያዩ የልማት ስራዎች በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን እየደገፈ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።