ኢትዮጵያ እና ኬንያ የኃይል ሽያጭ ስምምነት ተፈራረሙ

27/07/2022 12:53
ኢትዮጵያ እና ኬንያ የኃይል ሽያጭ ስምምነት ተፈራረሙ
ኢትዮጵያና ኬንያ ሲያደርጉት የነበረውን የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ድርድር አጠናቀው ትናንት ማምሻውን ስምምነት ፈጽመዋል። ስምምነቱን የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የኢፌዲሪ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በተገኙበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እና የኬንያ ኤሌክትሪክ መብራትና ኃይል ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጎፌሪ ሙሊ ተፈራርመዋል። በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ አሁን ላይ 200 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለኬንያ በሽያጭ ለማቅረብ ያስችላታል፡፡በቀጣይ ደግሞ ኢትዮጵያ ለኬንያ የምታቀርበውን የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን እስከ 400 ሜጋ ዋት ከፍ ለማድረግ ያለመ መሆኑም ተመልክቷል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር እያካሔደች የምትገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነት በሀገራቱ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ትስስር ይበልጥ እንዲጠናከር ከማድረጉም ባሻገር ፋይዳው የጎላ እንዲሆን ማድረጉም ተገልጿል። ኢትዮጵያ ቀደም ሲልም ከሱዳን እና ጅቡቲ ጋር የኃይል ሽያጭ እያካሄደች ሲሆን ከሶማሌ ላንድ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ግብረመልስ
Top