ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን ስለ 129ኛው የዓድዋ ድል በዓል ምን አሉ?

3 Days Ago 132
ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን ስለ 129ኛው የዓድዋ ድል በዓል ምን አሉ?
ኢትዮጵያ ክብሯን ያስጠበቀችበት፣ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠችበት እንዲሁም በቅኝ ግዛት ለነበሩ ሀገራት የነጻነት ተምሳሌት የሆነችበት የዓድዋ ድል በዓል በየዓመቱ ይከበራል።
 
ዘንድሮ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት የተከበረው 129ኛው የዓድዋ ድል በዓል በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን ሰፊ ሽፋን ተሰጥቶታል።
 
የድል በዓሉን አስመልክቶ የባህሬኑ ደይሊ ትሪቢዩን፣ የኬንያው ኔሽን፣ የፈንሳዩ ኤፒኤ እንዲሁም የናይጄሪያው ቢዝነስ ደይሊ ሰፊ ሽፋን ከሰጡ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን መካከል ናቸው፡፡
 
"የዓድዋ ድል የአፍሪካ የፀረ ቅኝ ግዛት ትግል ታሪክ ተምሳሌት ነው" በሚል ርዕስ ዘገባውን ያጋራው የፈንሳዩ ኤፒኤ፤ኢትዮጵያ የአውሮፓ ቅኝ ገዢ ወራሪውን ጣሊያን በማሸነፍ ነፃነቷን አስጠብቃ መቆየት የቻለች ብቸኛ ሀገር ናት ብሏል፡፡
 
በወቅቱ ኢትዮጵያውያን ዓርበኞች ወራሪውን ጣሊያን ድባቅ በመምታት ክብራቸውን ማስጠበቅ በመቻላቸው ደማቅ ታሪክ መፃፍ ችለዋል ነው ያለው በጽሑፉ፡፡
 
ቅኝ ገዢ አውሮፓውያን አፍሪካን ተከፋፍለው ሐብቷን ለመቀራመት በበርሊን ኮንፈረንስ መወሰናቸውን የተቃወመችው ኢትዮጵያ፤ጣሊያንን በማሸነፍ ነፃነቷን ከማስጠበቅ ባለፈ አህጉሪቱ ከቅኝ ግዛት እንድትላቀቅ ገንቢ ሚና ስለመጫወቷ አስነብቧል፡፡
 
ኢትዮጵያ ሉዓላዊነፃነቷን በማስጠበቅ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁ ያደረገ ድል ነው ሲል በዘገባው አስፍሯል።
 
"የጥቁር ህዝቦች ድል" በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በተከበረው 129ኛው የዓድዋ ድል በዓል የቀድሞው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ማህማትን ጨምሮ የሌሎች መሪዎች ንግግርን አካቶ ሰፊ ሀተታ ፅፏል፡፡
 
የባህሬኑ ደይሊ ትሪቢዩን በበኩሉ፤በባህሬን የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንፅላ፣ ኮሚዩኒቲ እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች የዓድዋ ድል በዓልን ማክበራቸውን አስነብቧል፡፡
 
ወጣቱ ትውልድ ከዓድዋ ጀግኖች ተምክሮ በመውሰድ በሀገር ግንባታ ገንቢሚና መጫወት መቻል እንዳለበት በበዓሉ ላይ መገለፁን አትቷል፡፡
 
በዓሉ ባዛር፣ የእግር ኳስ ውድድር፣ ሙዚቃ እና ሌሎች ዝግጅቶችን አካቶ በደማቅ ሁኔታ መከበሩን የባህሬኑ ደይሊ ትሪቢዩን ዘግቧል፡፡
 
የዓድዋ ድል በዓል በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መከበሩን የዘገበው ደግሞ የኬንያው ኔሽን ጋዜጣ ነው፡፡
 
የዓድዋ ድል የአፍሪካ ሀገራት በአንድነት ቆመው ኢ-ፍትዊነትን እንዲታገሉ ማንቂያ ደውል መሆኑን በመድረኩ መገለፁን አስነብቧል፡፡
 
ኢትዮያውያን አርበኞች ለሀገራቸው የነበራቸውን ቁርጠነት እና ጀግንነት የአፍሪካ ሀገራት መማር እንደሚችሉም ነው ጋዜጣው ያስነበበው፡፡
 
የዓድዋ ድል የአውሮፓን ቅኝ ገዢዎችን የበላይነት ትርክት በማፍረስ አፍሪካውያን ቅኝ ግዛትን እንዲታገሉ ማነቃቂያ መሆኑንም የኬንያው ኔሽን አክሏል፡፡
 
የናይጄሪያው ቢዝነስ ደይሊ በበኩሉ፤ የዓድዋ ድል አፍሪካ ማሸነፍ እንደምትችል ሕያው ማሳያ ነው፤ አህጉሪቱ ድሉን በኢኮኖሚ ዘርፍ መድገም ለምን አልቻለችም በሚል ርዕስ ሰፊ ሀተታ አስነብቧል፡፡
 
በላሉ ኢታላ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top