ፕሬዚደንት ታየ አጽቀ ሥላሴ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት /ተመድ/ ዋና ፀሐፊ አንቶንዮ ጉተሬዝን በፅሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይታቸውም በሀገራዊ፣ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
ፕሬዚደንት ታየ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እየተከናወነ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን ለዋና ፀሐፊው ገልፀውላቸዋል።
ተመድ ለኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች እያደረገ ያለውን ድጋፍ ያደነቁት ፕሬዚዳንቱ፤ ተለዋዋጭ በሆነው የወቅቱ ዓለም አቀፍ ሁኔታ ኢትዮጵያ የምታደርገው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶንዮ ጉተሬዝ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እየተከናወነ የሚገኘው አካታች ሀገራዊ ምክክር በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መገንዘባቸውን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም መስፈን እያደረገች ያለውን ጥረት አንቶንዮ ጉቴሬዝ አድንቀዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሀገራዊ፣ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።