38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ እና 46ኛው የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ በሰላም እንዲጠናቀቅ የፀጥታና ደኅንነት ጥምር ኃይል በቂ ዝግጅት አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቋል።
የፀጥታና ደኅንነት ጥምር ኃይል እስከ አሁን ድረስ በአዲስ አበባና በሀገር ዓቀፍ ደረጃ የተከናወኑ የፀጥታ ስራዎች ስኬታማ መሆናቸውን መገምገሙ ተገልጿል።
38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እና 46ኛው የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ በሰላም እንዲጠናቀቅ አዳዲስ ሎጅስቲክ አቅሞችን በመጠቀም፤ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፀጥታ ኃይል በማሰማራት በቴክኖሎጂ የታገዘ የፀጥታና የደኅንነት ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።
በተከታታይ እየተካሄደ ያለው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፤ ብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት፣ የሪፐብሊካን ጋርድ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና ሌሎች አጋር የፀጥታ አካላት የተቀናጀ ኦፕሬሽን አዲስ አበባ ከተማ ፍፁም ሰላማዊ ሆና እንድትቀጥል ያስቻለና አሁን ላይ የከተማዋ ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ መቀጠሉን በግምገማው ያረጋገጠ መሆኑን ጥምር ኃይሉ አመላክቷል።
ባካሄደው ግምገማ ለተገኘው ሰላም እና በተካሄደው ኦፕሬሽን ለተገኘው ውጤት የህዝቡ ተሳትፎ ከፍተኛ ነበር ብሏል።
አዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ ሕብረት እና የተለያዩ የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በመሆኗ ፀጥታዋ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥልም ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ በግምግማው መነሳቱ ተጠቅሷል።
እንደ ሀገር ሁሉም የፀጥታ መዋቅር የሚመለከተውን የሥራ ድርሻ ወስዶ አካባቢውን ፍፁም ሰላማዊ ለማድረግ በኃላፊነትና በተጠያቂነት የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ የፀጥታና ደኅንነት ጥምር ኃይሉ ጨምሮ ገልጿል።
በጉባኤው ላይ የሚታደሙ እንግዶችን በኢትዮጵያዊ ወግና ባሕል በመቀበል እና በማስተናገድ በቆይታቸዉ ጊዜ በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ፤ ካረፉባቸው ሆቴሎች ወደ መሰብሰቢያ አዳራሽ በሚሄዱበት ወቅት ሰላም ወዳዱ ሕዝብ በባለቤትነት የሚጠበቅበትን የዜግነት ድርሻውን በኃላፊነት እንዲወጣና ለፀጥታ አካላት እያደረገ ያለውን ቀና ትብብርም አጠናክሮ እንዲቀጥል የፀጥታና ደኅንነት ጥምር ኃይል ጥሪ አቅርቧል።