ኢትዮጵያ ለሱዳን ሰላም እና መረጋጋት ድጋፍ ማድረጓን ትቀጥላለች፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

1 Day Ago 150
ኢትዮጵያ ለሱዳን ሰላም እና መረጋጋት ድጋፍ ማድረጓን ትቀጥላለች፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ኢትዮጵያ ለሱዳን ሰላም እና መረጋጋት ድጋፍ ማድረጓን አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።

በኢትዮጵያ፣ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ በአፍሪካ ኅብረት እና በኢጋድ ቅንጅት የተዘጋጀ ለሱዳን ሕዝብ የሰብዓዊ ድጋፍ ማቅረብ ላይ ያተኮረ ከፍተኛ ኮንፈረንስ ተካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ ለሱዳን ህዝብ ሰላም እና መረጋጋት በሁሉም መስክ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከሱዳን ህዝብ ጎን ትቆማለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለሱዳን ሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት በሚደረገው ጥረት ላይ የበኩሏን ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል።

በመድረኩ 14 ሚሊዮን ሱዳናውያንን ያፈናቀለው የእርስ በእርስ ግጭት በመባባሱ ከ30 ሚሊዮን በላይ የሃገሪቱ ዜጎች የዕለት ደራሽ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተጠቁሟል።

ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ኢትዮጵያ የ15 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የ200 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ አድርገዋል።

የተደረገው ዕርዳታ ተደራሽ እንዲሆን በተጨማሪም ለመጪው የረመዳን ፆም የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ሀገራቱ መክረዋል።

በመድረኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጨምሮ፣ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ማህመት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በአፎሚያ ክበበው


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top