የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን እና የዳኞችን ሹመት በማጽደቅ ተጠናቋል።
ምክር ቤቱ በአራተኛ ቀን የጉባኤ ውሎው የቀረቡለትን ረቂቅ አዋጆች እና ረቂቅ ደንብ መርምሮ አጽድቋል።
በዚህም የክልሉን ፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ ረቂቅ አዋጅ፣ የባሕል ፍርድ ቤቶችን ለማቋቋም እና ዕውቅና ለመስጠት የወጣ ረቂቅ አዋጅ፣ ፍትሕ እና የሕግ ኢንስቲትዩት እንደገና ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ እና የፍርድ ቤቶች የዳኝነት አገልግሎት ክፍያ ለመወሰን የወጣ ረቂቅ ደንብን መርምሮ አጽድቋል።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ የክልሉ ፍርድ ቤት ዳኞችን ሹመት ያጸደቀ ሲሆን፣ 9 ዳኞች ለጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ሦስት ዳኞች ለከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንት፣ 46 ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች እና 171 ዳኞች ለወረዳ ፍርድ ቤት ዳኞች ሆነው መሾማቸውን አሚኮ ዘግቧል።
ምክር ቤቱ ከባድ የሥነ-ምግባር ጥሰት የፈጸሙ ሁለት ዳኞችን ለሦስት ዓመታት ከሥራ አግዷል።
የክልሉ ምክር ቤት የቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥም ዛሬ ተጠናቅቋል።
ምክር ቤቱ በተለይም በግጭት የተፈተነውን የክልሉን የትምህርት ዘርፍ መደገፍ እና ከትምህርት የራቁ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት ማምጣት በቀጣይ በትኩረት እንዲሠራበት አሳስቧል።