ኢትዮጵያ በታሪኳ የሰውን በመንካት አትታወቅም ከቅርብም ይሁን ከሩቅ የነኳትን ግን አሳፍራ መሸኘት ታሪኳ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሉዓላዊነት ቀንን አስመልክቶ ለሀገር ክብርና ሉዓላዊነት ዋጋ የከፈሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን በሚዘክረው መርኃ-ግብር ላይ በመገኘት መልክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው ትልቅ አቅም ያለው መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለወንድም ሀገራት ሉዓላዊነት ለመላው የሠው ዘር አንድነት ዋጋ መክፈል ልማዱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር መርህን መሠረት ያደረገ በሠላምና መረጋጋት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ትብብርና ግንኙነት ስትተገብር መቆየቷንም ነው ጠቅላይ ሚንስትሩ የተናገሩት፡፡
ለዚህም ባለፉት 6 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከጎረቤት ሀገራት ጋር አንድም ጥይት ተተኩሶ አለማወቁ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል፡፡
“ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከነጻነት ከክብር ልቆ ከመታየት ራስን አሳልፎ ከመስጠት ጋር የተያያዘ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ድጋፍ ለሚፈልጉ ወንድሞቻችን ሁሉ ከጎናቸው ቆመን ደግፈናቸዋል” ብለዋል፡፡
“ኢትዮጵያ ከማንም ጋር የመጋጨት ፍላጎትና ዓላማ የላትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ነገር ግን በቅርብም በሩቅም ያሉት ሊገነዘቡ የሚገባው ጉዳይ የሠው ነገር አንፈልግም በጥቅማችን ለሚመጡ ግን አሳፍረን ከመመለስ ወደ ኋላ አንልም” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን ለመንካት የፈለገ አንድ ብቻ አይደለም ከአስር ጊዜ በላይ ደጋግሞ ማሠብ ይገባዋልም ነው ያሉት በመልእክታቸው፡፡
የኢትዮጵያ ዓላማ ለራስ ህዝብ የልማት ትልሞችን ማሳካት እና በትብብር አብሮ ማደግ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ዳር ድንበርን ከማስጠበቅ ባለፈ ሁሉም ዜጋ በተሠማራበት ዘርፍ የኢትዮጵያን ከፍታ ለማረጋገጥ በትጋት በመስራት ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትን ማስጠበቅ እንደሚቻልም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡
በሮዛ መኮንን