ዩኒቨርሲቲው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ እና ልዩ ብቃት ያላቸው ተማሪዎች ማስተማሪያ ተቋም ይሆናል፡- የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

4 Mons Ago 418
ዩኒቨርሲቲው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ እና ልዩ ብቃት ያላቸው ተማሪዎች ማስተማሪያ ተቋም ይሆናል፡- የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2017 የትምህርት ዘመን በራሱ መመዘኛ ተማሪዎችን እንደሚቀበል አስታወቀ።

በትምህርት ዘመኑ ለዩኒቨርሲቲው በመንግስት በኩል የሚደረግለት የተማሪዎች ምደባ አለመኖሩንም ነው  ያስታወቀው።

የዩኒቨርሲቲው ተ/ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ዛሬ ለመገናኛ ብዙኀን በሰጡት መግለጫ፤ ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የቅድመ እና ድህረ ምረቃ ተማሪዎችን  ብቃትን መሰረት ባደረገ መልኩ በራሱ መመዘኛ የሚቀበል ይሆናል ብለዋል።

በሀገራዊ ፈተናው 50 በመቶ እና ከዛ በላይ ውጤት ማምጣት አንዱ መስፈርት ይሁን እንጂ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አቅምና ብቃትን ብቻ መሰረት ያደረገ ቅበላ ለማድረግ ተጨማሪ የመግቢያ ፈተና እንደሚሰጥ ነው የገለጹት።

አሰራሩ በመንግስት ወጪ የሚሸፈን የትምህርት እድል (ስኮላርሺፕ) እና በግል ወጪን በመሸፈን የተማሪዎችን ስብጥር በጠበቀ መልኩ ማስተናገድ እንዲቻል ተደርጎ የተቀረፀ ነው።
 
ዩኒቨርሲቲው አፍሪካዊ የሆነ ስመጥር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን እየሰራ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም፣ በተለይ ለጎረቤት ሀገራትና በኢትዮጵያ ተጠልለው ለሚገኙ ስደተኞች ቅድሚያ በመስጠትም ተማሪዎችን እንደሚቀበል ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል።
 
ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከሀገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል።
 
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ነፃነትን መሬት ላይ በማውረድ፣ ፍትሃዊ እና ብዝኀነትን በማስተናገድ ብቃትና አቅምን መሰረት በማድረግ በየዓመቱ እስከ 5 ሺህ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎችን ለመቀበል ይሰራል ብለዋል።
 
በአለም ይልፉ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top