የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) መመዘኛዎችን በሚያሟላ መልኩ የማጠናቀቂያ ስራዎች እየተከናወኑለት እንደሚገኝ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።
መንግስት ለስታዲየሙ ግንባታ አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግም ሚኒስትሯ አመልክተዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምን ጎብኝተዋል።
ስታዲየሙ የፊፋ መመዘኛዎችን በሚያሟላ መልኩ ጥራቱን ጠብቆ የማጠናቀቂያ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል መንግስት ስታዲየሙ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ በጀት በመመደብና ልዩ ትኩረት በመስጠት እያከናወነ ያለው ተግባር የሚደነቅና ለሌሎች ተምሳሌት የሚሆን ተግባር ነው ብለዋል።
ስታዲየሙ የስፖርት ቱሪዝምና የክልሉን ምጣኔ ሃብት ማሳደግ የሚያስችል አቅም ያለው መሆኑንም አመልክተዋል።
የፌዴራል መንግስት የባህር ዳርን ጨምሮ ለሌሎች ስታዲየሞች ግንባታ አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው ሚኒስትሯ የገለጹት።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ. በ2029 37ኛውን የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ማቀዷን የጠቆሙት ሚኒስትሯ ውድድሩን ለማስተናገድ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች ያስፈልጉናል ብለዋል።
ተጀምረው የቆዩ ስታዲየሞችን ለማጠናቀቅ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም የሁሉም ባለድርሻ አካላት ልዩ ትኩረት እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ቅጥር ግቢ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) መመዘኛን መሰረት በማድረግ በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ ቀሪ የማጠናቀቂያ ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የስታዲየሙ ሁለተኛ ምዕራፍ አካል የሆነው የማጠናቀቂያ ስራ የሜዳ ጥራት ማሻሻያ፣ የእንግዳ መቀበያ ክፍል፣ መቀመጫ ወንበር መግጠም፣ መሰብሰቢያ አዳራሽና ሌሎች ተግባራትም የሚከናወኑበት ነው።