የሰላም ሚኒስቴር ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የ7ኛው ሀገር አቀፍ የሰላምና ፀጥታ ምክክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
በሰላም ሚኒስቴር የ2016 በጀት ዓመት ሀገር አቀፍ የሰላም ግንባታና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት ላይ በመድረኩ ውይይት እንደሚደረግ ተመላክቷል።
በፌዴራሊዝም፣ በመንግስታት ግንኙነትና በግጭት አስተዳደር ዙሪያ የተከናወኑ ተግባራት ሪፖርት ቀርቦ ምክክር እንደሚደረግበትም ተጠቁሟል።
እንዲሁም በሰላምና ፀጥታ ተቋማት እየተሰሩ የሚገኙ ተግባራት የመስክ ምልከታ እንደሚካሄድም ይጠበቃል።
በተጨማሪም የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ በመወያየት ማጽደቅና ቀጣይ አቅጣጫ እንደሚቀመጥም ተመልክቷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የእውቅና አሰጣጥና ሌሎችም መርሐ-ግብሮች እንደሚኖሩ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።
በመርሐ-ግብሩ የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሳውን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።