ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት ስራ ላይ የተረባረቡ አካላትን ሁሉ አመስግነዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት፤ ከተሞቻችንን ለወደፊቱ ለዜጎቻችን ክብር የሞላበት የኑሮ ዘይቤን ለማጎናፀፍ የሚመቹ እንዲሆኑ ማዘጋጀት ይኖርብናል ሲሉ ገልፀዋል።
ከተሜነት እየተስፋፈ የሚሄድ መሆኑ የታወቀ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እኛም ዘላቂ እና ምቹ ከተሞችን ለመፍጠር ሁሉም መሳሪያዎች አሉን ሲሉ አክለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኮሪደር ልማት ስራው ላይ የተረባረቡ አካላትን ያመሰገኑ ሲሆን፤ የዛሬው የእውቅና መርሃግብር የተሻለ የከተማ ከባቢ ለመፍጠር ያሳያችሁትን ትጋት እና ጠንካራ ሥራ የሚያንፀባርቅ ነው ብለዋል።
ከመጀመሪያው የሥራ ምዕራፍ ብዙ ትምህርቶች ቀስመናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን ለሚቀጥለው ምዕራፍ ባላሰለሰ የመሻሻል ሂደት እና የሥራ ሥነምግባር በቀደመው ያሳካነውን ለማላቅ ተነስተናል ሲሉ ገልጸዋል።
ዛሬ የአዲሶቹን ኮሪደሮች ልማት በይፋ ስናስጀምር ልማቶቹ እና ጥገናዎቹ ከደረስንበት ምዕራፍ አልፈው የሚሻገሩ መሆናቸውን ማስታወስ ይገባናልም ብለዋል።
በተጨማሪም ይህን ጠቃሚ ሥራ ለማስፋፋት በምናደርገው ጥረት የተሰሩት ኮሪደሮች የሥራ መሪዎች በመላው ሀገራችን ተመሳሳይ ሥራ ለጀመሩ አስራ አንድ ከንቲባዎች ረዳት በመሆን ያገለግላሉ ሲሉ አክለዋል።