በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ ዘላቂ መፍትሔ እንደሚፈልግ የአደጋው ተጎጂዎች ገለጹ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በደቡብ ኦሞ ዞን ለኦሞ ወንዝ ገባር በሆኑ አካባቢዎች (በላይኛው ተፋሰስ) ሰሞኑን የጣለውን ከፍተኛ ዝናብ ተከትሎ፣ በዝቅተኛ ስፍራ በሚገኘው ዳሰነች ወረዳ የጎርፍ አደጋ ተከስቷል።
በወረዳው ባለፉት 8 ዓመታት በተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋ ተከስቶ በ34 ቀበሌዎች የሚኖሩ ከ79 ሺህ 828 በላይ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል።
የጎርፍ አደጋው ከነዋሪዎች መፈናቀል ባለፈ፣ የእንስሳት ሞትን ጨምሮ በእርሻ መሬት እና በንብረት ላይ ጉዳት አስከትሏል።
የዳሰነች ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ሐቴ በተለይ ለኢቢሲ ሳይበር አንደገለፁት፤ ዘንድሮ የጣለው ከባድ ዝናብ ከዚህ ቀደም ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠላያ ጣቢያ ይኖሩ የነበሩትን ጨምሮ 2ሺህ 744 ሰዎችን አፈናቅሏል።
ተፈናቃዮች ተጠልለውባቸው ከነበሩ 12 ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች መካከል ስምንቱ በዘንድሮው የጎርፍ አደጋ ስጋት ላይ መሆናቸው ተጠቁሟል።
የወረዳው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ብዙአየሁ ከበደ በበኩላቸው፤ዘንድሮ የጣለው ከባድ ዝናብ በኦሞ ወንዝ እና በቱርካና ሐይቅ ባስከተለው ሙላት ምክንያት የተከሰተው የጎርፍ አደጋ ነዋሪዎችን ስጋት ላይ እንደጣላቸው ገልጸዋል።
በወረዳው ኦሞራቴ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ናኮራ ሉሉክ ለኢቢሲ ሳይበር እንደገለጹት፤"የኦሞ ወንዝ ሞልቶ ያስከተለው ጎርፍ አስጨንቆናል፣ እርሻችን በጎርፍ ተውጧል ብለዋል፤ የጎርፉ ውኃ ወደ ከተማዋ ሊገባ ነው" በሚል ስጋት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዮሴፍ ሰቦቃ በሰጡት አስተያየት፤ ነዋሪዎች የጎርፉን ውኃ ለመገደብ ጥረት እያደረጉ ቢሆንም፤ የጎርፉ መጠን የሚጨምር ከሆነ፣ በጥቂት ቀናት ውስጥ የከተማዋን ነዋሪዎች ሊያፈናቅል ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
የወረዳው አስተዳደር ኦሞራቴ ከተማን ጨምሮ በርካታ ቀበሌዎችን ከጎርፍ አደጋው ለመከላከል ከተወሰኑ አካላት ጋር በመተባበር ውኃውን የመገደብ ስራ እየሰራ ቢሆንም ችግሩ ከአቅሙ በላይ መሆኑን ገልጾ፤የክልል እና የፌዴራል መንግስትን እገዛ እንደሚሻ ጠቅሷል።
ለጎርፍ አደጋው ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት በላይኛው ተፋሰስ የውኃ ማስተንፈሻ መስራት እንዲሁም ውኃውን ለመስኖ መጠቀም የሚቻልበትን መንገድ መቀየስ እንደሚገባ የወረዳው አስተዳደር ገልጿል።
ከ79 ሺህ 828 በላይ ተፈናቃዮች ከክልል እና ከፌዴራል መንግስት የእለት ደራሽ ምግብና አልባሳት እየረቀቡላቸው መሆኑን የዳሰነች ወረዳ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አስታውቋል።