የሰው ልጅ ከሌሎች ፍጥረታት ከሚለይበት ባህሪያቶች ውስጥ አንዱ ሀሳብ እና ስሜቱን በንግግር መግለጽ መቻሉ ነው።
አንደበት የመልካም እና የክፉ፣ የሚገነባ እና የሚያፈርስ፣ የሚተክል እና የሚነቅል፣ የሚያበረታ እና የሚያደክም፣ ተስፋ የሚሞላ እና ተስፋ የሚያስቆርጥ የውስጣዊ ተቃርኖ መፍሰሻ ቦይ ነው።
አንደበትን መግዛት ከሰውም ከፈጣሪም ጋር ተስማምቶ መኖሪያ አይነተኛ ጥበብ በመሆኑ ከመናገር በፊት ማስተዋል እንደሚገባ ቅዱሳን መጽሐፍት ይመክራሉ።
ከአፍ የወጣ ቃል እንደተሰነዘረ ሰይፍ ከማቁሰል መመለሻ ብልሐት የለውም፤ የሰይፍ ቁስል ሲውል ሲያድር ሲሽር በክፉ ቃል የሚፈጠር ቁስል ግን ጠባሳውን ከአይምሮ ለመፋቅ በእጅጉ ይፈትናል።
ኢትዮጵያዊያን ስድብ እና ክፉ ቃልን የሚያነውሩ፣ ቁጥብ ንግግርን እንደ መልካም እሴት የያዙ፣ ወንድምን እንደ ራስ በመውደድ ሌላው ላይ ያልተገባ ነገር ከማድረግ በመከልከል ወርቃማ ሰማያዊ ትዕዛዛት የኖሩ ህዝቦች ናቸው።
እኚህ ትዕዛዞች ከአካላዊ ጥቃት ባለፈ ባልንጀራን በክፉ ንግግር ከማቁሰል ከመቆጠብ ጋር ሰፊ ተዛምዶ እንዳላቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሰባኬ ወንጌል የሆኑት ዲያቆን አቤል ካሳሁን ይናገራሉ። ዲያቆን አቤል መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያዘው “ሰው ሁሉ ለማዳመጥ የፈጠነ ለመናገር (ለመቆጣት) ደግሞ የዘገየ መሆን አለበት” ይላሉ።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ም/ፕሬዚዳንት ሼህ አብዱልከሪም ሼህ በድረዲን በበኩላቸው፣ ቅዱስ ቁርአን “በአላህ እና በመጨረሻዋ ቀን (በቂያማ ቀን) ያመነ ሰው ጥሩ ነገር ይናገር ወይንም ዝም ይበል” እንደሚል በመግለጽ ሰዎች መልካም ነገር መናገር ቢያቅታቸው እንኳን ክፉ ነገር ከመናገር መቆጠብ እንዳለባቸው ያስገነዝባሉ።
ሰባሪ ቃላትን እያወጡ ሰዎችን መጉዳት የመንፈሳዊ ህይወት መሰንጠቅ (ስብራት) ምልክት መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ መጋቢ ቸርነት በላይ (ፓስተር ቸሬ) ናቸው። ፓስተር ቸሬ “በሰው ምላስ ላይ ህይወትም ሞትም፣ በረከትም እርግማንም አለ” በማለት ሰዎች መልካሙን መርጠው እንዲጠቀሙ ያሳስባሉ።
የስነ ምግባር እና ግብረ ገብ እሳቤዎች የተወለዱት ከኃይማኖቶች የጋራ እሴቶች ነው፤ እኚህ እሴቶች ከህግ እና ስልጣኔ በፊት ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት በጋራ እንዲኖሩ አስችለዋል። ፈጣሪን እና የመጨረሻዋን ቀን ፍርድ መፍራት ግፍን እና ስርዓት አልበኝነትን ለማረቅ በእጅጉ አግዟል። ስለ መልካም እና ክፉ ምላስም ዕለት ዕለት በየቤተ እምነቶች ተሰብኳል።
ሼህ አብዱልከሪም ከሰዎች አፍ የሚወጣው እያንዳንዱ ቃል ተመዝግቦ እንደሚቀመጥ በመግለጽ፤ አንደበት የሰዎችን ዘላለማዊ ህይወት ጭምር ሊወስን እንደሚችል ያስረዳሉ።
ዲያቆን አቤል ንግግርን በተመለከተ “ከሰሚው ሰው ይልቅ ተናጋሪው ሰው ይበልጥ ኃላፊነት እንዳለበት ተፈጥሮ እራሷ ታስተምረናለቸ” ይላሉ። “ዓይናችንን ማየት ባልፈለግነው ጊዜ መክደን ስንችል ጆሯችንን ግን ልንከፍተው እና ልንዘጋው አንችልም” በማለት ሀሳባቸውን ያስረግጣሉ።
የዲያቆን አቤልን ሀሳብን የሚያጠናክሩት ፓስተር ቸሬ “ሰው በአፉ የሚፈሰው በውስጡ የሞላው ነው” በማለት በተለይ “እኔ አፌ ነው እንጂ ውስጤ ባዶ ነው” የሚሉ ሰዎችን “ከአንደበት ኃጢያት” እራሳቸውን እንዲጠበቁ ይመክራሉ። ሰዎችን የሚገድለው እና የሚያቆስለው ጥይትም ከተተኮሰ በኃላ ውስጡ ባዶ እንደሆነ በምሳሌ ያስረዳሉ።
ባለንበት ዘመን በተለይ የማህበራዊ የትስስር ገጾች መስፋፋትን ተከትሎ ስድብ እና ተሳዳቢዎች አደባባይ ወጥተዋል። ቤተ እምነቶች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ወላጆች፣ መሪዎች በአጠቃላይ የማይሰደብ አካል የለም። ክፉ ንግግር በቀላሉ መታወቂያ እና በቶሎ መክበሪያ ሁነኛ አቋራጭ መንገድ ተደርጎ የተያዘም ይመስላል።
ነውር እና ብልግና ይህን ጉልበት ያገኙት ለቃላት ይሰጥ የነበረው ዋጋ እያነሰ በመምጣቱ እንደሆነ ዲያቆን አቤል ይናገራሉ። አበው የመጽሐፍ ቅዱስን “አትግደል” የሚለውን ትዕዛዝ ከሚተረጉሙበት አንድምታ ውስጥ አንዱ “ሰዎችን በመጥፎ ቃላት አትሰበር” የሚለው መሆኑን በማንሳትም በተለይ ብዙኃን ላይ ክፉ ቃላትን የሚናገሩ ሰዎች ብዙ ሰዎችን እንደመግደል የሚቆጠር ኃጢያት እየሰሩ መሆናቸውን ሊረዱት እንደሚገባ ያበክራሉ።
ፓስተር ቸሬ ትውልድ የሚያድግበትን የስነ ምግባር መሬት በግዴለሽነት መተዋችን ዋጋ እያስከፈለን መሆኑን ይጠቅሳሉ። “አሁን የምናያቸው አረም የሆኑ አዳዲስ ባህሎች እና የመጥፎ ቃላት ወረርሽኞች በሙሉ ያለመስራት ውጤቶች በመሆናቸው ሰው ወደ ቤቱ ተመልሶ ልጆቹን የሚባል እና የማይባል እንዲሁም የሚደረጉ እና የማይደረጉ ነገሮችን እንደ አዲስ ማስተማር አለበት” ይላሉ።
ሼህ አብዱልከሪም ልዩነትን በተገራ መንገድ ማቅረብ እና መፍታት ለሚቻልባቸው የምክክር፣ የሽምግልና እና ይቅር የመባባል መንገዶች ትኩረት መስጠት እንደሚገባም በአጽኖት ያነሳሉ። ቁርአን ከባለትዳሮች ጸብ ብዘሃንን እስከሚያሳትፉ አለመስማማቶች ድረስ እንዴት በሽምግልና እንደሚፈቱ በግልጽ እንደሚያስቀምጥም ያነሳሉ።
ያልተገቡ፣ የማያንጹ፣ ሀሰት የሆኑ፣ ሰዎችን ለክፉ ድርጊት የሚያነሳሱ እና የሚከፋፍሉ ንግግሮችን ያለ ኃፍረት እና ፍርሃት የሚናገሩ ግለሰቦች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ ሰባኪዎች፣ ፖለቲከኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች መበራከት በህዝቦች መካከል አለመተማመንን፣ መናናቅን፣ መጠራጠርን እና ጥላቻን እየፈጠሩ ይገኛል።
ያለ መልካም ቃል መከባበር፣ ያለ መከባበር መደማመጥ፣ ያለ መደማመጥ መግባባት፣ ያለ መግባባት ለአንድ ዓላማ መቆም፣ ያለ አንድ ዓላማ ጠንካራ ሀገር መገንባት አይታሰብም።
በእዮብ መንግስቱ