አሜሪካዊው ሴናተር ቦብ ሚኒንዴዝ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲደረግ ከግብጽ ጉቦ በመቀበላቸው ጥፋተኛ ተባሉ

4 Mons Ago 913
አሜሪካዊው ሴናተር  ቦብ ሚኒንዴዝ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲደረግ ከግብጽ ጉቦ በመቀበላቸው ጥፋተኛ ተባሉ
አሜሪካዊው ሴናተር ቦብ ሚኒንዴዝ በቀጣዩ ህዳር ወር በሚካሄዳው የአሜርካ ምርጫ እንደማይሳተፉ እየተነገረ ነው፡፡
 
በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር እንዲያስችላቸው በኒውጄርሲ በንግድ ስራ ላይ ከተሰማሩ 3 የግብጽ ሰዎች እጅ ወርቅና ጥሬ ገንዘብ ጉቦ መቀባላቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
 
ይህም ሴናተሩ ራሳቸውን ለግብጽ መንግሥት ወኪል አድርገው በመቆም ሰርተዋል የሚል ክስ ሲቀርብባቸው ነበር።
 
ሴናተር ቦብ ሚኒንዴዝ በዘረፋ፣ ጉቦ በመቀበል፣ ስልጣንን አላግባብ በመጠቀም፣ በሴራ፣ ፍትህን በማደናቀፍና መሰል 16 ወንጀሎች ተሳትፎ አድርገዋል በሚል ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው መሆኑንም ተመላክቷል፡፡
 
በመሆኑም በሚቀጥለው ህዳር ወር በሚካሄደው የአሜርካ ምርጫ ዴሞክራቶችን ወክለው የሚወዳደሩት ቦብ ሜኒዴዝ ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው እንዲለቁ ጥሪ የተደረገላቸው ሲሆን በሌላ እጩ እንደሚተኩም ነው የተገለጸው፡፡
 
የ70 ዓመት አዛውንቱ ቦብ ሚኒንዴዝ ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን ከሀገሪቱ ወታደራዊ እርዳታ ለመውሰድ አመቻችተዋልም ተብለዋል።
 
አጋሮቻቸውን ከወንጀል በመከላከል፣ አለአግባብ እንዲበለጽጉ በባለቤታቸው በኩል ከግብጽ የደህንነት ሰዎች ጋር ግኑኝነት በመፍጠር ስልጣንን አላግባብ ተጠቅመዋል ሲል አቃቤ ህግ ክስ መስርቶባቸዋል።
 
የውጭ ጉዳይ ግኑኝነት ቋሚ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር ሆነው ስራቸውን እየሰሩ ስለመሆናቸው የሚናገሩት ቦብ ሚኒንዴዝ በተጠረጠሩበት ወንጀል ለ9 ሳምታት ምርመራ ሲደረግባቸው ቢቆይም አልፈጸምኩም እያሉ ይገኛሉ፡፡
 
ሴናተሩ “እኔ በህዝብ ፊት የገባሁትን ቃል አልጣስኩም፣ ከሀገር ወዳድነቴና አርበኝነቴ ውጭ ምንም አልሆንኩም፡፡ለማንም ሀገር የምሰራው ጉዳይ የለኝም” ብለዋል፡፡
 
አሜርካዊው ሴናተር በተጠረጠሩበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የማምሻ እድሜያቸውን አስርት ዓመታት ወደ ማረሚያ ቤት ሊያመሩ እንደሚችሉ አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።
 
በመሀመድ ፊጣሞ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top