በ33ኛው የፓሪስ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በአንድ ወርቅ እና በሶስት የብር ሜዳልያዎች ከዓለም 47ኛ እንዲሁም ከአፍሪካ አራተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች።
ውጤቱም ሆነ ከውጤቱ በኋለ የነበሩ ሁነቶች በሙሉ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድም ቅሬታን እና ቁጭትን የፈጠሩ ሆነዋል።
ታዲያ ብዙ በተጠበቅንበት የፓሪስ ኦሊምፒክ ተሳትፎ ዙሪያ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴም በዛሬው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በመግለጫው ላይ አጠቃላይ የፓሪስ ቆይታን በተመለከተ በቴክኒክ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ቢልልኝ መቆያ አጠር ያለ ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን በሪፖርቱም ካለፉት ሁለት ኦሊምፒኮች የተሻለ ውጤት መገኘቱ ተገልጿል።
የተገኘው ውጤት የሀገራችንን የኦሊምፒክ ታሪክ የሚገልፅ አይደለም እና ተቋሙ ኃላፊነት ይወስዳል ወይ በተጨማሪም የኦሊምፒክ ኮሚቴው አመራሮች እራሳችሁን ከስልጣን ታነሳላችሁ ወይ በሚል ለቀረበው ጥያቄ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ፤ ለውጤት መጥፋቱ ሁሉም ኃላፊነት አለበት፤ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ያለአግባባ በማይመለከተው ጉዳይም እየተተቸ ይገኛል ብለዋል።
ስልጣንን በመልቀቅ እና በመሸሽ መፍትሔ ስለማይመጣ ከስልጣን የምለቅበት ምንም አይነት ምክንያት የለም ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በመልቀቄ የመጣ ለውጥ የለም ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም ኦሊምፒክ ተሳትፎ ነው ብዬ ለሰጠሁት ሀሳብ የቃሉ አውድ ለህዝባችን አዲስ ስለሆነ ይቅርታ እጠይቃለሁ፤ ነገር ግን የአለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ፅነሰ ሀሳብ የአትሌቶች ተሳትፎ ነው በሚል ስለሚገልፅ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ከአትሌቶች እና ከአሰልጣኞች ምርጫ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሙሉ ኃላፊነት ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሰጠ ቢሆንም የመጨረሻ ተወዳዳሪዎችን ምርጫ ላይ በጋራ መሰራቱን አንስተዋል፡፡
በዚህም በአትሌቶች ሰዓት እና በአሰልጣኞች ምርጫ ላይ የተደረጉ አንዳንድ ውሳኔዎች ዋጋ ማስከፈላቸውን ተናግረዋል።
በአብርሀም አድማሱ