በኢትዮጵያ ለመሬት መንሸራተት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው?

1 Mon Ago 280
በኢትዮጵያ ለመሬት መንሸራተት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው?
በኢትዮጵያ የስምጥ ሸለቆ ተጓዳኝ የሆኑ አካባቢዎች ለመሬት መንሸራተት ተጋላጭ እንደሆኑ የተደረጉ ጥናቶች ያመላክታሉ።
 
በዋናነት በምዕራብ ከፍተኛ ተራራማ ክፍል፣ በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከፍተኛና ተራራማ ስፍራዎች ለመሬት መንሸራተት ተጋላጭ እንደሆኑ ነው ጥናቶች የሚያመላክቱት።
 
ከዚህ ጉዳይይ ጋር በተገናኘ ከኢቢሲ ሳይበር ጋር ቆይታ ያደረጉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂዮ ፊዝክስ፣ስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ ተቋም ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ኤልያስ ሌዊ፤ በኢትዮጵያ በረጅም ዘመን የሚከሰት የተፈጥሮ አደጋ ጉዳትን ለመቀነስ ያለመ ስራ ያስፈልጋል ብለዋል።
 
ተቋሙ ባደረገው ጥናት 49 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ክፍል ለከፍተኛ፣ መለስተኛ እና አነስተኛ የመሬት መንሸራተት ተጋላጭ ስለመሆኑ ተመላክቷል።
 
በአቀማመጣቸው ተዳፋት በሆኑ አካባቢዎች ሰው ሰራሽ በሆኑ ድርጊቶች እና ከባድ ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት የመሬት መንሸራተት ሊከሰት እንደሚችል ነው ፕሮፌሰር ኤልያስ የሚናገሩት።
 
የመሬት መንሸራተት ተጋላጭነት ከታወቀ የአኗኗርን ዘይቤን ከአካባቢው ጋር ለማስማማት እና የሚደረጉ ግንባታዎችንም በጥንቃቄ ለማከናወን ያስችላል ይላሉ፡፡
 
የመሬት መንሸራተትና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች የሚያስከትሉትን ጉዳት ለመቀነስ ምን ማድረግ ይገባል በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ ፕሮፌሰር ኤልያስ ምላሽ ሰጥተዋል።
 
በምላሻቸውም፤ ለተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭ በሆኑ ቦታዎች በርቀት ዳሰሳ እና በአካል ክትትል ማድረግ፣ የቅድመ ዝግጁነት ጊዜ ማስጠንቀቂያ መረጃ ለህብረተሰቡ ማድረስ እንዲሁም ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ማድረግ ከባለሙያዎች የሚጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
 
ለመሬት መንሸራተት ተጋላጭ በሆኑ ቦታዎች የእርሻ ስራን አለማከናወን፣ ዛፎችን አለመመንጠር፣ ተራራማ ስፈራዎችን ከእንሰሳት ንክኪ መጠበቅ ደግሞ ከህብረተሰቡ የሚጠበቅ ተግባር ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡
 
የመሬት መንሸራተት ወይም መሰንጠቅ አደጋ አንዳንድ ጊዜ ምንም ምልክት ሳይታይ ሊከሰት እንደሚችል የሚናገሩት ፕሮፌሰር ኤልያስ፤ ከባድ ዝናብ ከጣለ በኋላ ከተራራዎች ስር ምንጭ መፍለቅ መጀመር ለመሬት መንሸራተት መከሰት ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል ብለዋል፡፡
 
ከዚህ አልፎ ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት ሲከሰት በእውቀት እና በባለሙያዎች ታግዞ ድጋፍ በማድረግ ተጨማሪ አደጋ እንዳይከሰት ማድረግ ተገቢ መሆኑን አሳስበዋል።
 
በላሉ ኢታላ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top