የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ለተፈናቀሉ ወገኖች 2.5 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ምግብ እና ምግብነክ ያልሆኑ ድጋፎችን አድርጓል።
ድጋፉን የኢቢሲ ልዑካን ሳውላ በመገኘት ያስረከቡ ሲሆን፤ በጎፋ ዞን በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል።
ኢቢሲን ወክለው ድጋፉን ያስረከቡት በኢቢሲ የሁነት ማስተባበሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ነጻነት ክንፈ፤ተቋሙ ለኢትዮጵያውያን መረጃ ከማድረስ ባሻገር መሰል ተፈጥሮአዊ አደጋዎች ሲደርሱም ሰብዓዊ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
በቀጣይም አቢሲ ለተጎጂዎች የሚደረገውን ድጋፍ የሚዲያ ሽፋን ከመስጠት ጀምሮ ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳግማዊ አየለ፤ኢቲቪ አደጋው ከደረሰ ጀምሮ ለሰራው ስራ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በቀጣይም የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ሁሉም ርብርብ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው።
በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም እስከ 350 ሚሊዮን ብር የሚጠይቅ በመሆኑ፤ ሁሉም ህዝብ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል።