የአማራ ክልልን ሰላም ለማረጋገጥና አሻጋሪ ልማቶችን በውጤት ለመፈጸም የአመራሩ ቁርጠኝነትና ዲስፕሊን ወሳኝ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
የአማራ ክልል ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2017 ዕቅድ የውይይት መድረክ መካሄድ ጀምሯል።
በውይይቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ፣ የክልሉ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ የአማራ ክልልን ሰላም ለማረጋገጥና አሻጋሪ የልማት ውጤቶችን ለማስመዝገብ አመራሩ በቁርጠኝነትና በዲሲፕሊን ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት በ2016 በጀት ዓመት በግጭት ውስጥም ሆኖ በርካታ የልማት ሥራዎችን ማከናወኑን ጠቅሰዋል።
ለአብነትም በፌደራል መንግሥቱ የተገነቡ አዲሱ የዓባይ ድልድይ፣ የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርትና ሌሎችንም ጠቅሰዋል።
በግብርናው መስክም ትልቅ ውጤት መምጣቱን አንስተው፤ በገቢ አሰባሰብ በችግር ውስጥ ሆኖ ከባለፈው በጀት ዓመት የተሻለ ገቢ መሰብሰቡን ገልጸዋል።
በ2017 በጀት ዓመትም ክልሉን ከነበረበት ነባራዊ ችግር ለማሻገርና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተዘጋጀውን ዕቅድ በአግባቡ መተግበር ከአመራሩ ይጠበቃል ነው ያሉት።
ዕቅዱን በአግባቡ ለመፈጸም የክልሉ አመራር በዲሲፕሊን መምራት ቁርጠኛ መሆን እንዳለበት አንስተዋል።
በዕቅዱ የተለዩ ፀጋዎችን በማልማት ወደ ሀብት ለመቀየር ውጤት ተኮር የሆነ አደረጃጀትንና የአመራር ስልትን መከተል ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በመሆኑም በአዲሱ በጀት ዓመት የተጀመረውን ሠላምና ልማት አጠናክሮ በመቀጠል የክልሉን ዕምቅ አቅምና ተስፋ ወደተጨባጭ ውጤት መቀየር እንደሚገባ አሳስበዋል።