በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ በተፈጸመ ዝርፊያ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንዳጋጠመው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሕግ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ አበበ ተስፋ እንደገለጹት በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ እየተፈጸመ ያለው ዝርፊያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።
በ2016 ዓ.ም ብቻ ከሦስት መቶ በላይ ዝርፊያዎች የተፈጸሙ ሲሆን ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በተቋሙ ሃብት ላይ ኪሳራ መድረሱን ጠቁመዋል።
በተቋሙ ላይ ከሚደርሰው ጉዳት በተጨማሪ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ሲዘረፉ በዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው ብለዋለ።
በቅርቡም ህገ-ወጦች "የተቋሙ ሰራተኞች ነን ቆጣሪ እናስገባ" በሚል ከስምንት ደንበኞች ከ30 እስከ 40ሺህ ብር የሚደርስ ገንዘብ ከተለያዩ አካባቢዎች ሲቀበሉ የነበሩ ህገ-ወጦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።
ፍርድ ቤት ቀርበው ጥፋተኝነታቸው ተረጋግጦ የ18 ዓመት ጽኑ እስራትና የ20 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ እንደተወሰነባቸው አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ በህገ ወጥ መንገድ ቆጣሪ ለማስገባትና ያልተገባ ጥቅም በመጠየቅ ተሳትፈው የተገኙ ሶስት የተቋሙ ሰራተኞች አስተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድ ከስራ እንዲሰናበቱ ተደርጓል ብለዋል።
በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ እየተፈጸመ ያለው ዝርፊያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንና አሳሳቢ መሆኑን ጠቁመዋል።
በበጀት ዓመቱ ከተፈጸሙ ከሶስት መቶ በላይ ወንጀሎች ውስጥ በ31 ግለሰቦች ላይ ብቻ ከአንድ ዓመት እስከ አስራ ስምንት ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት እንደተፈረደባቸው ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ይህም ወንጀል ፈጻሚዎችን ተከታትሎ ተገቢውን ፍርድ መስጠት ላይ ያለው ውስንነት የወንጀል ፈጻሚዎቹ ቁጥር እንዲበራከት እያደረገ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በቀጣይም ስርቆት በተደጋጋሚ የሚፈጸምባቸው አካባቢዎች ተለይተው ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱን ነው የገለጹት።
ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን መጠበቅ የአንድ ተቋም ሃላፊነት ብቻ አለመሆኑን ተረድተው፤ ወንጀልን በመከላከል ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የኢትዮ ቴሌኮም እና የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን ሁሉም ሰው እንዲጠብቅ የሚያስገደድ አዋጅ 1997/464 መውጣቱ ይታወቃል።