የብልጽግና ፓርቲ በብሪክስ ማዕቀፍ አማካኝነት የዓለምን ስርዓት ፍትሐዊና አሳታፊ ለማድረግ አበክሮ እንደሚሰራ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
በአቶ አደም ፋራህ የተመራ የልዑካን ቡድን በሩሲያ ቭላዲቮስቶክ በተጀመረው የብሪክስና አጋር አገራት ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፎረም ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
ፎረሙ “ወርልድ ማጆሪቲ ፎር መልቲፖላር ኦርደር” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ነው።
አቶ አደም ፋራህ በፎረሙ ላይ ባደረጉት ንግግር ፓርቲያቸው ብሪክስ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በቅርበት ሲከታተለው እንደቆየ ገልጸው ማዕቀፉ የዓለም የኢኮኖሚና ፖለቲካ ምህዳር የመቀየር አቅም እንዳለው ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል አገራትና ከአሰራር ማዕቀፉ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖራት እየሰሩ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ራዕይና አመራር ሰጪነት እንደ አገርም እንደ ፓርቲም ላለን ተሳትፎ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነውም ብለዋል።
ብሪክስ አዲስ አባል አገራትን ለማካተት በወሰደው ጠንካራ እርምጃ ምስጋናቸውን ያቀረቡት አቶ አደም ውሳኔው ኢትዮጵያ የጥምረቱ አባል እንድትሆን እድል ፈጥሯል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ የሆነው የብልጽግና ፓርቲ በአፍሪካ የተስፋና የለውጥ ብርሃን ነው ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ በመደመር እሳቤ በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ብልጽግና ለማምጣት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ፓርቲው ሕብረ ብሔራዊ አንድነት፣ ነጻነትና የዜጎች ክብር መሰረት አድርጎ መቋቋሙንና በፍጥነት እድገት በማሳየት ከ14 ሚሊዮን በላይ አባላትን ይዞ የአፍሪካ ትልቁ ፓርቲ መሆን መቻሉን ተናግረዋል።
ፓርቲው ኢትዮጵያውያንን ተሳታፊ በማድረግ በተለያዩ ዘርፎች አስደማሚ ውጤቶችን ማስመዘገቡንም ነው ያብራሩት።
በኢንዱስትሪ ልማት፣ በኢንፎርሜሽንና ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ ቱሪዝምና የማህበራዊ አገልግሎቶችን ጥራት ከማሳደግ አኳያም ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።
ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት የማከናወን ስራ አንዱ የብልጽግና ፓርቲ መገለጫ መሆኑን የገለጹት አቶ አደም ለዚህም የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በዋና ማሳያነት አስቀምጠዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ አገራት አንዷ መሆኗንና በአፍሪካም አምስተኛ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ እንደሆነች ጠቅሰዋል።
ስኬቶቹ የተመዘገቡት ኢትዮጵያ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች እየተፈተነች ባለበት ወቅት መሆኑንና ለውጤቱ መመዝብ ከፓርቲው አመራሮችና አባላት ያላሰለሰ ጥረት ባለፈ የኢትዮጵያ ሕዝብና አጋሮች ድጋፍ ቁልፍ ሚና እንደተጫወተ ነው አቶ አደም የገለጹት።
ብልጽግና ፓርቲ በአገራት ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነትና በሰላም አብሮ የመኖር እንዲሁም የባለብዙ ወገን ትብብርና ፍትሐዊ ዓለም በሚሉት ቁልፍ ምሰሶዎች ላይ የቆመ ነው ብለዋል።
በኢኮኖሚና ንግድ ትብብር ዘላቂ ልማትን ማምጣት ፓርቲው የሚደግፈው ሀሳብ መሆኑን ገልጸዋል።
ዓለም በብዙ አቅጣጫዎች ፍትሐዊ አይደለችም ያሉት አቶ አደም የዓለም የፋይናንስና የፖለቲካ ስርዓትና የብዙሃን መገናኛዎች ትርክቶች የዓለምን ብዝሃነት የሚያንጻባርቁ አይደሉም ብለዋል።
ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው የአፍሪካና የላቲን አሜሪካ አህጉራት እንደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት አለመወከላቸው ተገቢነት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም የአስተዳደር ስርዓት ይበልጥ አሳታፊና የዓለም ብዝሃነትን በማንጻባረቅ ሁሉን ያማከለ የብዝሃ ዓለም ስርዓት እንዲፈጠር ለሚደረጉ ማሻሻያዎች ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል።
ብሪክስ በሰላም፣ ኢኖቬሽን፣ ቴክኖሎጂና የጋራ ብልጽግና እውን ለማድረግ በአገራት መካከል ለሚከናወኑ የትብብር ስራዎች ወሳኝ ሚና እንዳለውና በዚህ ረገድም አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ነው ምክትል ፕሬዝዳንቱ የገለጹት።
የብሪክስ አባል አገራትና ሌሎች አጋር አገራት ማዕቀፉን በመጠቀም የጋራ ትብብርና አንድነትን ይበልጥ በማጎልበት የጋራ ተጽእኖ መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በትኩረት መስራት አለባቸው ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የብሪክስ አላማዎች እውን እንዲሆኑና የጋራ ግቦቹ እንዲሳኩ የበከሉን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አመላክተዋል።
በተጨማሪም ፓርቲው ብሪክስ የዓለም የፋይናንስ ስርዓት እንዲለወጥና ብዝሃነትን ማዕከል ያደረገ የዓለም ስርዓት እንዲፈጠር ለያዘው ግብ የበኩሉን ሚና ይወጣል ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ በቀጣይ ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሁለተኛ ጉባኤውን እንደሚያካሂድ ገልጸው በጉባኤውም ፓርቲው ባለፈው ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ያስመዘገባቸውን ስኬቶች በመገመገም ለቀጣይ ስራዎች አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥ ጠቁመዋል።
አቶ አደም በፎረሙ ላይ እየተካፈሉ ለሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጉባኤው ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረባቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።
የብሪክስና አጋር አገራት ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፎረም እስከ ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።