ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የቆየ ግንኙነትና ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች:- አቶ አደም ፋራህ

4 Mons Ago 411
ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የቆየ ግንኙነትና ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች:- አቶ አደም ፋራህ
ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የቆየ ግንኙነትና ትብብር በሁሉም ዘርፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።
 
በአቶ አደም ፋራህ የተመራ የልዑክ ቡድን ከሰኔ 9 እስከ 12/2016 በሚካሔደውና "ዎርልድ ማጆሪቲ ፎር መልቲፖላር ኦርደር" በሚል መሪ ቃል በሩሲያ ቪላዲቮስቶክ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፎረም ላይ እየተሳተፈ ነው።
 
ከፎረሙ ጎን ለጎን አቶ አደም ፋራህ ከቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ የዓለም አቀፍ ዘርፍ ሚኒስትር ሊዩ ጂንቻዎ ጋር ተወያይተዋል።
 
በውይይታቸውም ላይ አቶ አደም ቻይና በኢትዮጵያ ልማት ላይ ጠንካራ የኢኮኖሚ አጋር ሃገር መሆኗን አስረድተው በርካታ የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
 
ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜዎች ባጋጠሟት ፈተናዎች ሁሉ ቻይና የማይናወጥ አቋም ይዛ እያደረገች ላለው ድጋፍ ያመሰገኑት አቶ አደም በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለው የፖለቲካ ወዳጅነትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
 
ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ከፍተኛ ሚና ባለው ብሪክስ አባል ሀገር ለመሆን ያደረገችው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲሳካ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲና መንግስት ላደረጉት ድጋፍም አቶ አደም ምስጋና አቅርበዋል።
 
አቶ አደም አያይዘውም ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን ስትራተጂያዊ አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደምትሰራ ገልጸው፤ ሊዩ ጂንቻዎን ጨምሮ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ አመራሮች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ጋብዘዋል።
 
ሊዩ ጂንቻዎ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል በመሆኗ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው፤ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ ግንኙነትና ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።
 
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ማዕከል በመሆኗም ቻይና ከኢትዮጵያም አልፎ ከአፍሪካዊያን ጋር ለሚኖራት ትብብር ቁልፍ ሚና እንዳላት አስረድተዋል።
 
በመሆኑም የሁለቱን ሃገራት የቆየ ትብብር ከማሳደግ ባለፈ የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነቱን በልምድ ልውውጥ፣ በስልጠና ፕሮግራሞች እና በአቅም ግንባታ ዘርፍም አጠናክረው መቀጠል እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
 
ከዚህ ባለፈም በንግድና ኢንቨስትመንት ያለውንየሁለትዮሽ ግንኙነት ለማሳደግ ቻይና በትኩረት እንደምትሰራ ገልጸው፤ በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ትብብር የተገነባውን የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር በአብነት ጠቅሰዋል።
 
ሚኒስትሩ በመጨረሻም በመጪው ጥቅምት በሚካሔደው የቻይና አፍሪካ መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ልዑካን እንዲገኙ ግብዣ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top