አርሶ አደሩ ለማዳበሪያ ግዢ ሞባይል ባንኪንግን በመጠቀሙ ሕገወጥ የማዳበሪያ ሽያጭን ለማስቀረት ተችሏል፡- የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ

7 Days Ago
አርሶ አደሩ ለማዳበሪያ ግዢ ሞባይል ባንኪንግን በመጠቀሙ ሕገወጥ የማዳበሪያ ሽያጭን ለማስቀረት ተችሏል፡- የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ
አርሶ አደሩ ለማዳበሪያ ግዢ ሞባይል ባንኪንግን በመጠቀሙ ሕገወጥ የማዳበሪያ ሽያጭን ማስቀረት መቻሉን የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
 
የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የምርት ግብዓቶችን በጊዜው ለማቅረብ የተጠናከረ ሥራ እየሠራ መሆኑን እና በዚህም ውጤታማ እንደሆነ ገልጿል።
 
ለኢቢሲ ሳይበር አስተያየታቸውን የሰጡት በኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የምርት ማሳደጊያ ፍላጎት እና አቅርቦት ዳይሬክተር አቶ ታከለ ቁሩንዴ፤ ባለፈው ዓመት 7.5 ሚሊዮን ኩንታል የዐፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ማድረስ መቻሉን አስታውሰው፣ ፍላጎቱ እየጨመረ በመምጣቱ በዘንድሮው ዓመት 8.27 ሚሊዮን ኩንታል የዐፈር ማዳበሪያ ግዢ ተፈጽሟል ብለዋል።
 
ከዚህ ውስጥም 6.3 ሚሊዮን ኩንታል ወደ ሀገር መድረሱን እና ቀሪው እየተጓጓዘ መሆኑን ጠቅሰው፣ ያለፈውን ዓመት ጨምሮ 4.47 ሚሊዮን ኩንታል ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ተናግረዋል።
 
ዘንድሮ መንግሥት በሰጠው አቅጣጫ በመናበብ ለመሥራት በመቻሉ ግዢውም ሆነ ስርጭቱ ከአምናው በጣም የተሻለ ነው ያሉት አቶ ታከለ፤ አርሶ አደሩ ጋር የደረሰው የአፈር ማዳበሪያ እስካሁን ለተዘራው ሰብል እና እየተዘራ ላለው በቂ መሆኑን ተናግረዋል።
 
ሕገ ወጥ የማዳበሪያ ሽያጭን ለማስቀረት አርሶ አደሩ ክፍያውን በሞባይል ባንኪንግ እንዲፈጽም መደረጉን አውስተው፤ ይህም ሕገወጦች በማዳበሪያ ግብይት እንዳይገቡ እና ገንዘብም እንዳይባክን ማስቻሉን ገልጸዋል።
 
አርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ ላይ የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ አብዛኛው አርሶ አደር ጥሩ ግንዛቤ እያገኘ በመሆኑ ሞባይል ባንኪንግን እየተጠቀመ ነው ብለዋል።
 
የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎችም የአፈር ማዳበሪያ ለማድረስ ከሰላም አስከባሪ ኃይሎች ጋር በቅንጅት እየተሠራ በመሆኑ እስካሁን በፀጥታ ችግር ምክንያት ማዳበሪያ አልደረሰንም የሚል ቅሬታ አለመነሳቱን ገልጸዋል።
 
አቶ ታከለ እንዳሉት፤ ከማዳበሪያ በተጨማሪም 104 ሺህ 593 የበቆሎ ዘርን ጨምሮ ሌሎች አግሮ ኬሚካል ግብዓቶችም በሚያስፈልገው ሁኔታ እየቀረበ ነው።
 
አርሶ አደሩ ማዳበሪያ የሚቀርብለት በህብረት ስራ ማህበራት በኩል ብቻ መሆኑን አውቆ ከሕገ ወጦች ራሱን እንዲጠብቅ፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ተገዝቶ የተሰጠውን ማዳበሪያ በቁጠባ እንዲጠቀም፣ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ካላስፈላጊ የጊዜና ገንዘብ ብክነት እንዲጠበቅ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
 
በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top