የሽግግር ፍትሕ ማስተግበሪያ ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ተጠናቀቀ

11 Days Ago
የሽግግር ፍትሕ ማስተግበሪያ ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ተጠናቀቀ
የሽግግር ፍትሕ ማስተግበሪያ ፍኖተ ካርታ ዝግጅት መጠናቀቁን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ።
 
የፍትሕ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱ መጠነ-ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ውስብስብ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በወንጀል ተጠያቂነት፣ እውነትን ማፈላለግ፣ ይፋ ማውጣት እና ዕርቅ ማውረድ፣ በቅድመ-ሁኔታ ላይ በተመሰረተ ምህረት፣ በተቋማዊ ማሻሻያ እንዲሁም በማካካሻ ስልቶች ላይ የተዋቀረ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁን አስታውሷል፡፡
 
በፖሊሲው መሰረት ነጻ እና ገለልተኛ ተቋማት ተቋቁመው ሁሉንም የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የማስተግበሪያ ስልቶች ስራ ላይ እስኪያውሉ ድረስ የትግበራ ምዕራፉን የመጀመሪያ ዙር ስራ የማስተባበር ሚናውን ለመወጣት የትግበራ ሂደቱን የሚያመላክት ፍኖተ ካርታ ሲያዘጋጅ መቆየቱን ገልጿል።
 
በዚህም መሰረት በፖሊሲው የትግበራ ምዕራፍ የሚከናወኑ ተግባራትን በዝርዝር የያዘ ረቂቅ ፍኖተ ካርታ ተጠናቅቆ ለውይይት ዝግጁ መሆኑን ይፋ አድርጓል።
 
በፍኖተ-ካርታው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በአባልነት የሚሳተፉበት ጊዜያዊ እና ዘላቂ ተቋማዊ የቅንጅት አመራር ስርዓት ስለሚቋቋምበት ሁኔታ፤ ስለ ሽግግር ፍትህ ስልቶች አተገባበር ቅደም-ተከተል መካተቱን አንስቷል።
 
ተመጋጋቢነት እና ተደጋጋፊነት፤ ተቋማቱን ለማቋቋም እና ከተቋቋሙም በኋላ ስራቸውን ስለሚሰሩበት ሁኔታ የሚደነግጉ የህግ ማዕቀፎች ስለሚዘጋጁበት ሁኔታ እና የተቋማቱን አቅም ለመገንባት ስለሚሰሩ ስራዎች የሚያትቱ ዝርዝር ተግባራት ተቀርጸው ተቀምጠዋል ነው ያለው፡፡
 
ፍኖተ ካርታው በሽግግር ፍትሕ ትግበራ ምዕራፍ ሂደት የክልሎችን፣ የባህላዊ ፍትህ ስርዓቶችን፣ የተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ሚና፣ ተሳትፎ እና ኃላፊነት፣ እንዲሁም የፆታዊ ጥቃት ሰለባዎችን በተመለከተ የሚተገበሩ ተጨማሪ እርምጃዎችን በውስጡ እንዲይዝ መደረጉንም አብራርቷል።
 
በሌላ በኩል የሽግግር ፍትሕ በሀገር ወይም በመንግስት መሪነት እና ህዝባዊ ባለቤትነት መርህ የሚመራ ስርዓት እንደመሆኑ መጠን ፖሊሲውን ህዝባዊ ገፅታ ለማላበስ የፖሊሲውን አስፈላጊነት፣ ይዘት እና የትግበራ ሂደት በተመለከተ ሕዝቡ ያለውን እውቀት ለማሳደግ ስለሚሰሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ዝርዝር ተግባራት በፍኖተ ካርታው እንዲመላከቱ ተደርጓል፡፡
 
ከትግበራ ምዕራፍ ረቂቅ ፍኖተ ካርታው በተጨማሪ የሽግግር ፍትሕ ጊዜያዊ የተቋማት የቅንጅት አመራር ስርዓት ማቋቋሚያ ረቂቅ መመሪያ፣ የሽግግር ፍትሕ ስልቶች አተገባበር ቅደም-ተከተል ማብራሪያ ሰነድ መዘጋጀታቸውን ገልጿል።
 
የአጋር ተቋማት ግንኙነት እና ትብብር ማንዋል እና የሽግግር ፍትሕ ኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ ሰነዶች የተዘጋጁ ሲሆን ፖሊሲውን ወደ ተለያዩ ሀገር በቀል ቋንቋዎች የመተርጎም ስራ መጀመሩንም ጠቁሟል።
 
የእንግሊዝኛውን ቅጂ የማዘጋጀት ስራው ከእርማት በስተቀር በአብዛኛው መጠናቀቁንም ሚኒስቴሩ በመግለጫው ማንሳቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዚህም መሰረት የፍኖተ ካርታውን ረቂቅ ሰነድ ጨምሮ በተዘጋጁት የማስተግበሪያ ሰነዶች ላይ የሚደረጉ ውይይቶች ሲጠናቀቁ የፖሊሲው ትግበራ ምዕራፍ ዋና ዋና ተግባራት መከናወን እንደሚጀምሩ አረጋግጧል፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top