የብልፅግና ፓርቲ ለቤንች ብሄር የዘመን መለወጫ ባስተላለፈው የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት “በዓሉ ለመላው የብሄሩ ተወላጆችና ኢትዮጵያዊያን በሙሉ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የሰላምና የደስታ እንዲሆንላችሁ ፓርቲያችን ብልፅግና ከልብ ይመኛል።” ብሏል፡፡
የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
እንኳን ለቤንች ብሄር የዘመን መለወጫ እና የምስጋና በዓል (ቢስት ባር) አደረሳችሁ፣ አደረሰን!!!
የሰው ልጅ ኑሮውን የሕይወት ዑደቱን የሚገልፅበት የተለያየ ባህልና ስርዓት አለው።
በየሀገሩ ብንሄድ አየሩ አፈሩ ቀዬውና መንደሩ ልዩ ነውና የወቅቱን መፈራረቅ የአከባቢውን መልከዓምድር ውበት ለመግለፅ በየበአሉና እምነቱ ቀን ተመርጦና ተወስኖ ይከበራል።
ለዛም ነው በሀገራችን ኢትዮጵያ እንደየ አከባቢውና እንደየባህሉ ብዙ ልዩ የዘመን መሻገርያ ቀናትንና አስደናቂ ትውፊቶችን የምንመለከተው።
በሀገራችን ከሚገኙ የተለየ የዘመን መለወጫ ቀናት ካሏቸው ብሄረሰቦች መካከል የቤንች ህዝብ የዘመን መለወጫ ቀን "ቢስት ባር" አንዱ ነው።
በለምለሙና የምድር ገነት ተብሎ በተመለከቱት ሁሉ ስም የሚወጣለት ጣፋጭ ቡና አምራቹ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኘው የቤንች ህዝብ ዓመትን ጨርሶ ሌላ አዲስ ዓመትን የሚቀበልበትና ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት ቀን "ቢስት ባር" ይባላል።
በሀገሬው ቋንቋ "ቢስት" ማለት የመጀመርያ ወይም በኩር ሲሆን "ባር" ደግሞ በዓል ማለት ነው።
የመከበርያ ቦታውም የብሄረሰቡ ታሪካዊ መገኛ ቦታ ነው በሚባለው “ዣዣ” ሲሆን ይህም ቀደምት የነበሩ የብሄረሰቡ ተወላጆች ጠንካራና ስራ ወዳድ መሆናቸውን ለማሳየት በነሱ መገኛ ቦታ እንደሆነ በማሰብ የተደረገ ነው።
የቤንች ህዝብ "ቢስት ባር"ን ህዳር አጋማሽ ላይ ያከብራል። ለዚህም ምክንያቱ ክረምቱ ጨለማው ጭጋጉ አልፎ ሰማይ ጥርት ብሎ ሲገለጥ እህል ከተዘራበት ተሰብስቦ ሲቀመስ ብርሀን መጣ ጥጋብ ሆነ ተብሎ በማሰብ ነው።
ለ"ቢስት ባር" ዝግጅት የባህላዊ መጠጥ የበቆሎ ቦርዴ ስራ ቅደም ተከተሉን ጠብቆ ለበዓሉ ድምቀት ይሰናዳል።
ይህን የባህላዊ ምግብ አዘጋጆች ደግሞ እናቶች ናቸው::
የበቆሎ ቦርዴ ዝግጅቱን ድንጋይ ሰብስበው እንጨት ጨምረው በእሳት በማጋል ከታች ቅጠል እንዲሁም ከላይ ቅጠል ከመሀል በውሃ በማራስ በድንጋይ ወፍጮ የተፈጨውን የተለያየ ሂደትን ያለፈውን የበቆሎ ቡኮ በማድረግ የማብሰል ሥራ በባህላዊ ጭፈራ ታጅቦ የበቆሎ ቦርዴ ዝግጅቱ ይሰናዳል።
የቤንች ህዝብ የሚገኝበት ቤንች ሸኮ ዞን በቡና ምርት በተለያዩ የቅመማ ቅመም ምርት በተፈጥሮ የጫካ ማርም ታዋቂ ነው።
"ዲጋም ቢስት ባርሽን ይንት ሀትሳሲሴ"