ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሁለት ባለ 9 ወለል ዘመናዊ ሕንጻዎችን እና የስራ ዕድል መፍጠሪያ ማዕከላትን መርቀው ለአቅመ ደካሞች አስተላለፉ

3 Mons Ago 430
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሁለት ባለ 9 ወለል ዘመናዊ ሕንጻዎችን እና የስራ ዕድል መፍጠሪያ ማዕከላትን መርቀው ለአቅመ ደካሞች አስተላለፉ
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ "በጎነት" ተብሎ በተሰየመ የመኖሪያ መንደር የተገነቡ ሁለት ባለ 9 ወለል ዘመናዊ ሕንጻዎችን እና የስራ ዕድል መፍጠሪያ ማዕከላትን መርቀው ለአቅመ ደካሞች እና አካል ጉዳተኞች አስተላልፈዋል።
 
በመኖሪያ መንደሩ የተገነቡት ሁለት ባለ 9 ወለል ዘመናዊ ሕንጻዎቹ እና የስራ ዕድል መፍጠሪያ ማዕከላቱ ለ140 አቅመ ደካሞች እና አካል ጉዳተኛ ነዋሪዎች መተላለፋቸውን ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው አስታውቀዋል።
 
በልደታ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ቆርቆሮ ሰፈር በሚባለው የተጎሳቆለ የመኖሪያ መንደር ይኖሩ ለነበሩ አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ማየት ለተሳናቸው፣ ለተለያየ ማህበራዊ ችግር ለተጋለጡ እና በልማት ለተነሱ ነዋሪዎች የተላለፉት ምቹ የመኖሪያ ቤቶች፤ ሳሎን፣ መኝታ ቤት፣ የማብሰያ እና የመጸዳጃ እንዲሁም የመኝታ ክፍሎች ያላቸው ዘመናዊ ቤቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
 
በዚህ የ"በጎነት" መንደር ከተላለፉ የመኖሪያ ቤቶች ጋር በማቀናጀት የእናቶችን ጫና የሚያቀል የህጻናት ማቆያ፣ ለአካባቢው እናቶች የስራ ዕድል የሚፈጥር ዘመናዊ የእንጀራ መጋገሪያ፣ የሚሰሩ እጆችን ከስራ የሚያገናኙ የወንዶችና የሴቶች የውበት ሳሎኖችን እንዲሁም የልብስ ስፌት ማሽኖች ተዘጋጅተው ለነዋሪዎቹ የስራ እድል መፈጠሩንም ጠቁመዋል።
 
ከንቲባዋ በመኖሪያ መንደሩ ቤት ለተሰጣቸው ማየት የተሳናቸው ነዋሪዎች እንቅስቃሴ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ኬኖች፣ ለአካል ጉዳተኛ ነዋሪዎች ደግሞ ክራንችና ዊልቸሮችን አዳርሰናልም ነው ያሉት።
 
የሚሰሩ ልማቶች ሁሉ ለሰው ልጆች ተስፋ የሚሰጡ እና የኑሮ ጫናን የሚያቃልሉ ይሆኑ ዘንድ ሰው ተኮርነታችን በተግባር የሚገለጽ ነው ሲሉም ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡
 
ሰርቶ ካገኘው ላይ ለወገን በጎ ለመስራት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር ቤቶቹን የገነባውን ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በራሳቸውንና በነዋሪዎች ስም አመስግነዋል፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top